Sunday, September 22, 2024
spot_img

በጀርመናውያን ባለሐብቶች ሲተዳደሩ የነበሩ አራት ትምህርት ቤቶች ለቱርክ መንግሥት ተላልፈው ተሰጡ

አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ነሐሴ 8፣ 2013 ― በፌቱላህ ጉለን ንቅናቄ ስር የነበሩ እና በስተኋላ ለጀርመን ባለሐብቶች የተሸጡ፤ በአዲስ አበባ የሚገኙ አራት ትምህርት ቤቶች በቱርክ መንግስት ስር ላለ ተቋም ተላልፈው ተሰጥተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አፍሪካ ኅብረት፣ ሳር ቤት፣ ፈረንሳይ እና ሲ ኤም ሲ አካባቢዎች የሚገኙት አራት ትምህርት ቤቶች መጀመሪያ የተከፈቱት፤ መቀመጫቸውን በአሜሪካ ባደረጉት ቱርካዊ የእስልምና ሃይማኖት መምህር ፌቱላህ ጉለን ስም በተመሰረተው ‹‹የሂዝመት ንቅናቄ›› ነበር።

በ2008 በቱርክ ከተደረገው የከሸፈ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ጀርባ ፌቱላህ ጉለን ነበሩበት ሲል የወነጀለው የቱርክ መንግስት፤ ከዚያን ጊዜ ወዲህ ንቅናቄውን በአሸባሪነት ፈርጇል።

የቱርክ መንግስት በፍረጃ ብቻ ሳይወሰን በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ የንቅናቄው አባላትን በእስራት የቀጣ ሲሆን፣ የሀገሪቱ መንግስት ከጉለን እና ደጋፊዎቻቸው ጋር ንኪኪ አላቸው ያላቸውን በሌሎች ሀገራት የሚገኙ ድርጅቶችን እና ተቋማት ጭምር እንዲዘጉ አድርጓል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ በ160 ሀገራት በንቅናቄው የተከፈቱ የትምህርት ተቋማትንም፤ በቱርክ መንግስት ስር ወዳለው ‹‹ተርኪሽ ማሪፍ ፋውንዴሽን›› ለማዛዋወር ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። እንደ መንግስታዊው የቱርክ የዜና አገልግሎት አናዶሉ ዘገባ ከሆነ፤ የቱርክ መንግስት የማሪፍ ፋውንዴሽንን በ2008 ያቋቋመው፤ ‹‹ከፌቱላህ ጉለን አሸባሪ ድርጅት›› ጋር ግንኙነት አላቸው የሚላቸውን ትምህርት ቤቶች ለማስተዳደር ነው፡፡

በኢትዮጵያ ‹‹ነጃሺ ኢትዮ-ተርኪሽ›› በሚል ስያሜ ስር ተከፍተው አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩ፤ በጉለን ንቅናቄ ስር የነበሩ አምስት ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች ነበሩ። ከትምህርት ቤቶቹ ውስጥ አምስቱ ‹‹ስቲም ኤዱኬሽን›› ለተባለ የጀርመን ድርጅት በ2009 መሸጣቸው ውዝግብ ቀስቅሶ ቆይቷል። የይገባኛል ጥያቄው ፍርድ ቤት ጭምር የደረሰ ነበር።

አምስቱን ትምህርት ቤቶቹን የሸጠው፤ በቱርካውያን ባለሃብቶች የሚተዳዳረው ካይናክ የትምህርት እና ሕክምና ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር፤ ‹‹የተከተለው የሽያጭ ሂደት ህጋዊ አይደለም›› በሚል ነበር በፍርድ ቤት ክስ የቀረበው። ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክሱን የከፈተው የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ መሆኑንም ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ዘግቧል፡፡

የትምህርት ቤቶቹ የሽያጭ ሂደት ‹‹የቱርክ መንግስት በኢትዮጵያ የሚገኙት የካይናክ ንብረቶች ተላልፈው እንዲሰጡት ባቀረበው ጥያቄ መሰረት፤ ንብረቶቹ ወደ ቱርክ መንግስት እንዲተላለፉ ስራ እንዲጀመር መመሪያ ከተሰጠ በኋላ፤ የንብረቱን መወረስ ለማስቀረት በማሰብ በህገ-ወጥ መንገድ [የተከናወነ ነው]›› በማለት ዐቃቤ ህግ የጀርመኑ ድርጅት ንብረቶች እንዲታገዱ መጠየቁን በዘገባው ተመላክቷል፡፡

የአምስቱን ትምህርት ቤቶች ጉዳይ ሲመለከት የቆየው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት፤ ንብረቶቹ ታግደው እንዲቆዩ ትዕዛዝ አስተላልፏል። ዐቃቤ ህግ ከዚህ በተጨማሪም፤ በጀርመኑ ድርጅት ስር ያሉ ንብረቶች ላይ ሊደርስ የሚችለውን ‹‹ማናቸውንም ህገወጥ ተግባራት ለማስቀረት›› በሚል የንብረት አስተዳዳሪ እንዲሾም ጥያቄ አቅርቦ ነበር ነው የተባለው።

ይህን ጥያቄ የመረመረው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባለፈው ሰኞ ነሐሴ 3፤ 2013 ባዋለው ችሎት፤ የ‹‹ማሪፍ ፋውንዴሽን›› ንብረቶቹን ተረክቦ እንዲያስተዳድር ትዕዛዝ ሰጥቷል። የፍርድ ቤቱን ውሳኔን ተከትሎም በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ አራት ትምህርት ቤቶች ወደ ፋውንዴሽኑ መተላለፋቸው ነው የተነገረው፡፡

ሆኖም ‹‹ኢንተለክቹዋል›› የሚል ስያሜ የተሰጣቸውን ትምህርት ቤቶች ሲያስተዳድር የቆየው ‹‹ስቲም ኤዱኬሽን›› የተባለው ድርጅት የአስተዳደር እና የሰው ኃይል ስራ አስኪያጅ የሆኑት ሃካን አሉስ ግን ትምህርት ቤቶቹን ‹‹ከማሪፍ ፋውንዴሽን በመጡ ሰዎች ተቀምተናል›› ሲሉ ይወነጅላሉ። በትምህርት ቤቶቹ ቅጥር ግቢ ውስጥ የቱርክ ሰንደቅ ዓላማ መሰቀሉንም በማሳያነት ጠቅሰዋል።

ከአራት አመታት በፊት የተከናወነው የትምህርት ቤቶቹ ሽያጭ “ህጋዊ ነበር” ሲሉ የሚከራከሩት ሃካን አሉስ፤ “የጀርመን ባለሃብቶች በድርጅቶቹ ላይ ፍላጎት በማሳደራቸው ነው የተገዙት” ሲሉ ሂደቱ የ“ንግድ ውሳኔ” ብቻ እንደነበር ያስረዳሉ።

እርሳቸው ይህን ቢሉም፤ በስራ አስኪያጅነት የሚያገለግሉበት ድርጅት፤ በሰበታ አለም ገና ከተማ የሚገኘውን ሌላኛው የትምህርት ቤት ቅርንጫፉን ባለፈው ወር በፍርድ ቤት ትዕዛዝ አምጥቷል። ይህንኑ ቅርንጫፍ የ‹‹ተርኪሽ ማሪፍ ፋውንዴሽን›› ሐምሌ 7፤ 2013 ጀምሮ መረከቡን ማስታወቁ በዘገባው ተመላክቷል፡፡

የማሪፍ ፋውንዴሽን ባለፈው ወር እና በዚህ ሳምንት ከጀርመኑ ድርጅት ከተከረከባቸው አምስት ትምህርት ቤቶች በተጨማሪ፤ በሐረር ከተማ የሚገኝ በጉለን ንቅናቄ የተከፈተ ትምህርት ቤትንም ከሁለት ዓመት በፊት የመጠቅለል ዕድል አግኝቷል። “ሬይንቦው የበጎ አድራጎት ማህበር” በተባለ ድርጅት ስር ይተዳደር የነበረው ትምህርት ቤት፤ ከቅድመ መደበኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ድረስ የሚያስተምር ነው።

ከትምህርት ቤቱ በተጨማሪ ግንባታው አልቆ የህክምና ቁሳቁሶችን በማሟላት ላይ የነበረ የበጎ አድራጎት ማህበሩ ሆስፒታልም፤ ወደ ማሪፍ ፋውንዴሽኑ መተላለፉ ተነግሯል፡፡ “ማሪፍ አለም አቀፍ ትምህርት ቤት” የሚል አዲስ ስያሜን አግኝቶ ስራ ቢጀምርም፤ ሆስፒታሉ ግን እስካሁን ድረስ አገልግሎት መስጠት እንዳልጀመረ ነው የተሰማው፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img