Sunday, October 6, 2024
spot_img

በቱርክ አንካራ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከዛሬ ጀምሮ ለተገልጋዮች ክፍት እንደማይሆን ታወቀ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ነሐሴ 7፣ 2013 ― በቱርክ አንካራ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከዛሬ ነሐሴ 7፣ 2013 ጀምሮ ለተገልጋዮች ክፍት እንደማይሆን ታውቋል፡፡

አምባ ዲጂታል በተመለከተው የቆንስላው ደብዳቤ ከተጠቀሰው ቀን አንስቶ አዲስ ፓስፖርት ለማውጣት፣ የማደስ፣ የጠፋ የመተካት፣ ለኢትዮጵያውያን የመኖሪያ ፍቃድ መስጠት፣ የልደት እና ሞት ሠርተፍኬት እና የትብብር ደብዳቤዎችን ለሚፈልጉ ሰዎች አገልግሎት እንደማይሰጥ ነው የገለጸው፡፡

ኢትዮጵያ በቱርክ አንካራ የተገነባው አዲሱ ኤምባሲዋን ያስመረቀችው በተያዘው ዓመት የካቲት ወር ላይ የነበረ ሲሆን፣ በርካታ ገንዘብ ፈሶበታል በተባለው ሕንጻ ምርቃት ሥነ ሥርዓት ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን እና የቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜቩሉት ካቩሶግሉ ተገኝተው ነበር፡፡

በተመሳሳይ በኳታር ዶሃ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲም አገልግሎት ፈላጊ ዜጎችን ከትላንት ነሐሴ 6 ጀምሮ እስከ ነሐሴ 13 ድረስ ባለው ብቻ እንደሚያስተናግድ አስታውቋል፡፡ ኤምባሲው ይህንኑ በገለጸበት ደብዳቤው የፓስፖርት እድሳት ማድረግ የሚፈልጉና ከስድስት ወር ያነሰ እድሜ የቀረው ፓስፖርት ያላቸው ሰዎች በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ ብቻ እንደሚስተናገዱ ገልጧል፡፡

የዶሃ ኤምባሲ በደብዳቤው ከዚህ ቀደም እሰከ ጳጉሜ 2 ድረስ ቀጠሮ የተሰጣቸው ተገልጋዮች እንደነበሩ ያስታወሰ ሲሆን፣ ነገር ግን እነዚህ ባለቀጠሮዎች መስተናገድ የሚችሉት በአዲሱ የጊዜ ቀጠሮ ገደብ ብቻ መሆኑንም አስታውቋል፡፡

በተያዘው ዓመት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መዝጊያ እለት የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያ በተለያዩ አገራት ከሚገኙ ኤምባሲዎቿ መካከል ግማሽ ያህሉን ልትዘጋ እንደምትችል መናገራቸው አይዘነጋም፡፡ ለኤምባሲዎቹ መዘጋት የውጪ ምንዛሪ እጥረት አንዱ ቁልፍ ምክንያት እንደሆነ ተነግሯል።

ይህን ተከትሎ ከሰሞኑ እንዲመለሱ ታዘዋል የተባለው በጀርመን በርሊን ኤምባሲ የሚሠሩ ስድስት የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶችን ጨምሮ በሌሎች አገራት የሚገኙም ተመሳሳይ ትእዛዝ እንደደረሳቸው መዘገባችን የሚታወስ ነው፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img