Sunday, September 22, 2024
spot_img

አምነስቲ ኢንተርናሽናል በትግራይ ግጭት የተፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶችን የዳሰሰበትን የጥናት ውጤት ይፋ አደረገ

– ከየካቲት እስከ ሚያዚያ ባለው ወቅት ብቻ ከ1 ሺሕ በላይ ሴቶች መደፈራቸውን ሪፖርት ማድረጋቸውን አመልክቷል

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ነሐሴ 5፣ 2013 ― ዓለም አቀፉ የስብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል ስምንት ወራት ባስቆጠረው የትግራይ ክልል ጦርነት የተፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶችን የዳሰሰበትን የጥናት ውጤት ይፋ አድርጓል፡፡

አምነስቲ ለሪፖርቱ ከኅዳር እስከ ሰኔ ወር ድረስ 63 ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች ቃለ ምልልስ ማድረጉን የገለጸ ሲሆን፣ እነዚህ የጥቃት ሰለባዎች 15ቱን በሱዳን በስደተኛ መጠለያዎች በአካል፣ 48 ሴቶችን ደግሞ በስልክ ማግኘቱን አስታውቋል፡፡

ለሪፖርቱ ግብአት የሕክምና ባለሞያዎች፣ በሽረ እና አዲግራት ጥቃት ደረሰባቸው ድጋፍ የሰጡ የረድኤት ሠራተኞችን ማነጋገሩንም ነው የገለጸው፡፡

በዚሁ መሠረት ድርጅቱ ይፋ ባደረገው ባለ 39 ገጽ ሪፖርት ከተለያዩ የጤና ተቋማት ሰበሰብኩት ባለው መረጃ መሠረት ከየካቲት እስከ ሚያዚያ ባለው ወቅት ብቻ በጦርነቱ ውስጥ 1 ሺሕ 288 የሚሆኑ የአስገድዶ መድፈር ጥቃቶች የተፈጸመባቸው ተጠቂዎች ወደ ሕክምና መስጫ ተቋማት በማቅናት ሪፖርት ማድረጋቸውን አመላክቷል።

አምነስቲ አነጋግርኳቸው ካላቸው መካከል የጥቃቱ ሰለባዎች ውስጥ ብዙሃኑ ከአንድ በላይ በሆኑ ሰዎች ተገደው ተደፍረዋል። ከእነዚህ ውስጥ የተወሰኑት ነፍሰ ጡርና ኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ሲሆኑ፣ የተወሰኑት በልጆቻቸው ፊት ተገደው የተደፈሩ መሆናቸውን ሪፖርቱ በዝርዝር አስነብቧል።

አምነስቲ ካነጋገራቸው ሰዎች መካከል 38ቱ በቡድን የተደፈሩ ሲሆኑ፣ ከእነዚህ መካከል የባአከር ከተማ ነዋሪ የነበረች የ20 ዓመት ወጣት ሴት ትገኝበታለች።

አምነስቲ ባስነበበው የወጣቷ ቃል ‹‹ኅዳር 28 ወደ ቤታችን የጦር መሳሪያ እንፈትሻለን ብለው ሁለት የደንብ ልብስ የለበሱ እና አንድ ሲቪል ልብስ የለበሰ ታጣቂዎች መጡ›› ያለች ሲሆን፣ ‹‹አባቴም መተኛቴን ሲነግራቸው ሳይረብሹኝ ፈትሸው እንደሚወጡ ነግረውት ቤት ውስጥ ያሉ ሰዎችን አስወጥተው ወደኔ መጡ፤ ሲነጋገሩ ከእንቅልፌ ነቃሁ፤ ከዚያም ድምጽ እንዳላሰማ በምልክት አስጠንቅቀውኝ በየተራ ደፈሩኝ፤ የአራት ወር ነብሰ ጡር መሆኔን ይረዱ አይረዱ አላውቅም፤ ሰው መሆኔንም ይረዱ አይረዱ አላውቅም›› ማለቷም ተመላክቷል፡፡

በሪፖርቱ ለደኅንነቷ ሲባል ንግሥት የሚል ስም የተሰጣት የ25 ዓመት እናትም በሽራሮ ከተማ እርሷ እና ሌሎች አራት ሴቶች በኤርትራዊያን ወታደሮች መደፈራቸውን ተናግራለች። በተጨማሪም ከሁመራ በመሸሽ ላይ የነበሩት ንግሥት እና አብረዋት የነበሩት ሴቶች በቡድን መደፈራቸውንም ተናግራለች፡፡ ‹‹ከመሃላችን አንደኛዋ የስምንት ወር እርጉዝ ነበረች፤ ለአምስት ደፈሯት፤ በዚህ ምክንያት ልጇን ያለጊዜው ወለደች›› ብላለች፡፡

በሌላ በኩል የባድመ ከተማ ነዋሪ የነበረችው የምስራች ኤችአይቪ በደሟ ውስጥ እንደሚገኝ ብትገልጽላቸውም አራት የኤርትራ ወታደሮች አስገድደው እንደደፈሯት ሪፖርቱ አስነብቧል።

አምነስቲ ካነጋገራቸው 68 ሴቶች ውስጥ 12ቱ ለቀናት እና ለሳምንታት በቆየ የወሲብ ባርነት ውስጥ እንደነበሩ ገልጸዋል።

ከእነዚህ ውስጥ ሦስቱ ህጻናት ሲሆኑ አንዳንዶቹ በጦር ካምፖች፣ ሌሎቹ በመኖሪያ ቤቶች አንዲሁም በሜዳ ላይ ለቀናት ተይዘው መቆየታቸውን ተቋሙ ገልጿል።

በሪፖርቱ ላይ ተሳታፊ የሆኑት የአምነስቲ ከፍተኛ መርማሪ ዶናቴላ ሮቬራ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የኤርትራ እና የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት እንዲሁም የአማራ ኃይሎች ‹‹አጥቂ›› ተብለው በተጠቂዎች ተለይተዋል።

የጥቃቱ ሰለባዎች አጥቂዎቹን በሚናገሩት ቋንቋ እንዲሁም በደንብ ልብሳቸው እንደለዩ ዶናቴላ አክለዋል።

ጥቃቱን በተመለከተም ዶናቴላ ‹‹በመካከለኛው ምሥራቅ ብሎም በተለያዩ የአፍሪካ ክፍሎች ባሉ የግጭት አካባቢዎች ተዘዋውሬ የጾታ ጥቃቶችን መርምሬያለሁ። አሁን የሰማኋቸው ምስክርነቶች ግን እጅግ አስከፊው ናቸው›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አምነስቲ የኢትዮጵያ መንግሥት እና የተመድ የሕግ የበላይነት እና የጾታዊ ጥቃት ጉዳዮችን የሚመለከተው ቡድን ምርመራ አካሂደው ጥፋተኞች ለሕግ እንዲቀርቡ ጥሪ አቅርቧል።

አምኔስቲ ኢንተርናሽናል በሪፖርቱ ያወጣውን ግኝት በተመለከተ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ ከፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ፣ የሴቶች፣ ከሕጻናት እና ወጣቶች ሚኒስቴር፣ ከኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር እና ከሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ አማካሪ ማብራሪያ ቢጠይቅም ምላሽ አለማግኘቱን አሳውቋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img