Tuesday, October 15, 2024
spot_img

ኢሰመኮ በአፋር ሕፃናትን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ላይ ግድያ ተፈጽሟል መባሉን ተከትሎ የክትትል ቡድን ማሰማራቱን አስታወቀ

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ነሐሴ 5፣ 2013 ― የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሐምሌ 28፣ 2013 በአፋር ክልል ጉሊና ወረዳ ጋሊኮማ ቀበሌ በሚገኝ ጤና ጣቢያ እና ትምህርት ቤት ላይ በደረሰ ጥቃት በርካታ ቁጥር ያላቸው ሕፃናትን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች መገደላቸው ሪፖርት ከተደረገ በኋላ የክትትል ቡድን ማሰማራቱን አስታውቋል፡፡

ግጭት ባገረሸባቸው የአማራ ክልሎችም ክትትል እያደረገ እንደሚገኝ ያመለከተው ኮሚሽኑ፣በግጭቱ ሳቢያ አደጋ ውስጥ የወደቁ ሲቪል ዜጎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱና የሰብአዊ ርዳታ ፍላጎቱ እየተባባሰ በመምጣቱ እጅጉን እንዳሳሰበው ገልጧል፡፡

ኢሰመኮ ሀሉም በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ አካላት እና የፀጥታ ኃይሎች በሀገራዊም ሆነ በዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች እንዲሁም በጦርነት ሕግና መርሆች የተጣለባቸውን ግዴታ እንዲያከብሩ አሳስቧል፡፡

በተጨማሪም ሲቪል ሰዎችና ታሪካዊ ቅርሶችን ጨምሮ ሲቪል መሠረተ ልማቶች ኢላማ መደረግ እንደሌለባቸው የገለጸው ኢሰመኮ፣ ሕጻናት እና ተጋላጭ ማህበረሰቦች በማንኛውም ጊዜ ልዩ ጥበቃ ሊደረግላቸው የሚገባ የማህበረሰብ ክፍሎች ናቸው ብሏል፡፡

የተባበሩት መንግስታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) በአፋር ክልል በጤና ተቋም እና ትምህርት ቤት ውስጥ ተጠልለው የነበሩ ከ100 በላይ ህጻናትን ጨምሮ፤ 200 የሚልቁ ተፈናቃዮች ተገድለዋል መባሉን መግለጹ ይታወሳል፡፡

የደረሰውን ግድያ በተመለከተ የአፋር ክልል የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ባለፈው ዐርብ ሐምሌ 30 ባወጣው መግለጫ ለጥቃቱ የህወሓት ኃይሎችን ተጠያቂ አድርጎ የነበረ ቢሆንም፣ በሕወሓት በኩል ግን የተሰጠ ምላሽ የለም፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img