Monday, October 14, 2024
spot_img

መንግስት መከላከያ ሠራዊቱ የክልል ልዩ ኃይሎችና ሚሊሻዎች በህወሓት ኃይል ላይ እርምጃ እንዲወስዱ አቅጣጫ ሰጠ

አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ነሐሴ 4፣ 2013 ― የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ባስተላለፈው ጥሪ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ተነስቷል የተባለውን የሕወሓት ኃይል እና የውጭ እጆች ስውር ደባ ለመደምሰስ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የክልል ልዩ ኃይሎችና ሚሊሻዎች ብርቱና ‹‹የማያዳግም ክንዳችሁን እንድታሳርፉ›› የሚል አቅጣጫ መቀመጡን አስታውቋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በመግለጫው ‹‹ሀገር በመከላከል ዘመቻው ለመሳተፍ እድሜያችሁና ዐቅማችሁ የሚፈቅድላችሁ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የመከላከያ ሠራዊቱን፣ ልዩ ኃይሉንና ሚሊሻውን በመቀላቀል የሀገር ዘብነታችሁ የምታሳዩበት ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው›› ያለ ሲሆን፣ የጸጥታ ኃይሎችን በቀጥታ ለመቀላቀል ያልተቻለው የኅብረተሰብ ክፍል ከመቼም ጊዜ በላይ ወገቡን አሥሮ በልማት ሥራዎች ላይ ተሳትፎውን ማጠናከርእንዳለበት አሳስቧል፡፡

አክሎም የመንግሥት ሠራተኛውም በሙሉ ዐቅሙ ያለ ቢሮክራሲ ሥራውን እንዲያከናውን፣ ሁሉም ዜጋ ነቅቶ አካባቢውን እንዲጠብቅ፣ ‹‹የጁንታው ተላላኪዎች የጥፋት ተልዕኳቸውን እንዳይፈጽሙ ሕዝባችን በዓይነ ቁራኛ ይከታተል›› ብሏል፡፡

ከዚህ ባለፈ ለሠራዊቱ የሚሆን ስንቅ በማዘጋጀትና የሞራል ድጋፍ በማድረግ ብርቱ ደጀን ይሁን ያለው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ ‹‹ሚዲያዎች፣ የኪነ ጥበብ ባለሞያዎችና ማኅበራዊ አንቂዎች ሕዝቡ ከሀገሩ ጎን እንዲቆም የበኩላችሁን አስተዋጽኦ እንድታበረክቱ›› እንደሚጠበቅም ጠቅሷል፡፡

በተጨማሪም ‹‹አሸባሪው ጁንታ ሰላማዊ ሰዎች አስመስሎ በየአካባቢው ያሠማራቸው ሰላዮችና የጥፋት ተላላኪዎችን ለመከታተልና ለማጋለጥ እንዲቻል፣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለሀገሩ ዐይንና ጆሮ በመሆን ከጸጥታ አካላት ጋር በቅርበት ሊሠራ ይገባል›› ያለ ሲሆን፣ ‹‹የሃይማኖት አባቶች በጸሎት፣ የሐገር ሽማግሌዎች በምክር፣ ሁሉም ዜጋ በችሎታው ኢትዮጵያን ብሎ›› እንዲቆም ጠይቋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በመግለጫው ውጊያው ‹‹የትግራይ ሕዝብ ብሎም መላዋ ኢትዮጵያን ከአሸባሪው ቡድን ነጻ ለማውጣትና የሀገራችንን ሰላምና አንድነት ለማስከበር›› እንደሆነና ‹‹ትግላችን ከአሸባሪው ጁንታ ጀርባ ላይ ተፈናጥጠው ሀገራችንን ለማፈራረስና የኢትዮጵያን ህልውና ለማጨለም ከተነሡ የቅርብና የሩቅ ኃይላትና ሀገራት ጋር ጭምር›› መሆኑንም ነው ያመለከተው፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img