Sunday, September 22, 2024
spot_img

ኢትዮጵያ ወታደሮቿ በሰላም ማስከበሩ እንዳይሳተፉ መጠየቁ እንዳሳዘናት ገለፀች

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ሐምሌ 12፣ 2013 ― የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በትግራይ ጦርነት የተሳተፉ የኢትዮጵያ ወታደሮችን ከሰላም አስከባሪነት ሊያግድ ይገባል በሚል የአሜሪካ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ሊቀ መንበር መጠየቃቸው እንዳሳዘናት ኢትዮጵያ ገልፃለች።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከተመድ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ድጋፍ ሰጭ ዋና ኃላፊ አትዋል ካሬ ጋር በተነጋገሩበት ወቅት ነው ይህን ያሳወቁት።

የኮሚቴው ሊቀ መንበር ሴናተር ቦብ ሜንዴዝ ለተመድ በጦርነቱ የተሳተፉ ወታደሮች ይታገዱ ብለው ደብዳቤ መፃፋቸው ከማሳዘን በተጨማሪ ሰላምና ፀጥታን ለማስጠበቅ እያገለገሉ ያሉትን የኢትዮጵያ የሰላም አስከባሪ ኃይሎች አስተዋፅዖ ዕውቅና የነፈገ ነው ብለውታል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ።

ሴናተር ቦብ ሜንዴዝ በትግራይ ክልል ጦርነት የተሳተፉ የኢትዮጵያ ወታደሮች በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ አለመሳተፋቸው በአስተማማኝ የማጣራት ሂደት እስኪታወቅ ድረስ በተባበሩት መንግሥታት የሰላም ማስከበር ሥራዎች እንዳይሳተፉ በሚል ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ደብዳቤ መፃፋቸው መነገሩ የሚታወስ ነው።

በውይይቱ ወቅት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተባበሩት መንግስታት የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል አዎንታዊ ሚና እንዲሁም የኢትዮጵያ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ የቆየ ታሪክን አጉልተው በማንሳት ተነጋግረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በተጨማሪም የተባበሩት መንግሥታት የአብዬ ጊዜያዊ የፀጥታ ኃይል የተለያዩ ችግሮች ቢያጋጥሙትም በአብዬ ሰላምና እና መረጋጋትን ለማምጣት እጅግ ገንቢ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለተባበሩት መንግሥታት ቀጣይ ድጋፍ እንደምታደርግ ሚኒስትሩ ያረጋገጡ ሲሆን፣ ዋና ኃላፊው በበኩላቸው አገሪቷ በተባበሩት መንግስታት የሰላም ማስከበር ያላትን የተልዕኮ ሚናዋ አድንቀዋል።

ሴናተሩ ከሁለት ሳምንታት በፊት የኢትዮጵያ ወታደሮችን አስመልክቶ በፃፉት ደብዳቤ እንደ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር በመሳሰሉ ገለልተኛ ተቋማት የማጣራት ሂደት እስኪታወቅ ድረስ እግዱ ሊፀና ይገባል በማለት ጠይቀው ነበር።

በደብዳቤያቸው ላይ አክለውም ኢትዮጵያ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች በርካታ ቁጥር ያላቸውን ወታደሮች የምታዋጣ እንደመሆኗ መጠን የተባበሩት መንግሥታት በሰላም ማስከበሩ ላይ የሚሳተፉ የኢትዮጵያ ወታደሮች በትግራይ ወታደራዊ ዘመቻ ላይ ስለመሳተፋቸው ጠንከር ያለ የማጣራት ሂደት እንዲከናወን መጠየቃቸውም ሰፍሯል።

ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ስር በተለያዩ አገራት ውስጥ ለሚደረጉ የሠላም ማስከበር ተልዕኮዎች ከፍተኛ የሚባለውን ከ8 ሺህ 300 በላይ ሠራዊት ያበረከተች ሲሆን ከዚህም ውስጥ ከፍተኛው ቁጥር በሱዳን ውስጥ በሚገኙት ዳርፉርና በአብዬ ግዛት ውስጥ የተሰማሩ መሆናቸውም ይነገራል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በሶማሊያ የሰላም አስከባሪ ኃይል የስራ ድጋፍን በተመለከተ እንዲሁም በዳርፉርና ፣ በአብዬና በደቡብ ሱዳን ያለውን የፀጥታ ኃይሉን የስራ ጊዜ መጠናቀቅ አስመልክቶ ኃሳቦችን መቀያየራቸውንም የዘገበው ቢቢሲ ነው።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img