Sunday, October 6, 2024
spot_img

የሕወሃት ቡድንን በተግባር ይደግፋሉ ተብለው የተጠረጠሩ 323 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር እንዳዋለ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ

አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ሐምሌ 10፣ 2013 ― በሽብር የተፈረጀውን የሕወሃት ቡድንን በተግባር ይደግፋሉ ተብለው የተጠረጠሩ 323 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር እንዳዋለ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።

በአዲስ አበባ ከተማ አሸባሪውን የህወሃት ቡድንን በመደገፍ በተለያዩ የተግባር እንቅስቃሴዎች ተሰማርተዋል በሚል ወንጀል የተጠረጠሩ 323 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ደበላ ÷ከተጠረጠሩባቸው ወንጀሎች መካከል አሸባሪው የህወሀት ድርጅትን መደገፍ፣ የጦር መሳሪያ ይዞ መገኘት፣ ሕገመንግስቱን ማንቋሸሽ፣ ሰንደቅ ዓላማን ማዋረድ፣ ኃሺሽ ማጨስ እና ቁማር መጫወት ይገኙበታል።

በወንጀሎቹ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ከዋሉት ግለሰቦች መኖሪያ ቤት በፍርድ ቤት ፍቃድ በተደረገው ፍተሻ የህወሀት ልዩ ኃይል አልባሳት፣ ሽጉጦች፣ ክላሾች እና ጥይቶችን ጨምሮ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች በቤታቸው መገኘቱንም ኮሚሽነሩ ጠቅሰዋል።

ከተጠርጣሪዎቹ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ የንግድ ድርጅቶችም ታሽገው ምርመራ እየተካሄደ መሆኑንም ኮሚሽነር ጌቱ ገልፀዋል።

ተጠርጣሪዎቹ አንዳንድ አካላት እንደሚገልፁት በብሔራቸው ምክንያት ሳይሆን በቁጥጥር ስር የዋሉት በትክክልም ተጨባጭ ወንጀል ፈፅመው በመገኘታቸው መሆኑን ነው ኮሚሽነሩ የገለፁት።

አዲስ አበባ ከተማ የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ ከእንደዚህ አይነት ወንጀሎች ነፃ የሆኑት በርካታ የትግራይ ተወላጆች በነፃነት በከተማ ውስጥ እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ገልፀዋል።

ከተጠርጣሪዎች መካከል ከትግራይ ብሔረሰብ ውጪ የሆኑ የሌላ ብሔረሰብ አባላት እንደሚገኙበትም ኮሚሽነሩ አንስተዋል።

ከተማዋን የጥፋት ቀጠና ለማድረግ አሸባሪ ቡድኑን በመደገፍ የአገርን ሰላም ለማናጋት የሚያስቡ ካሉ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ያሳሰቡት ኮሚሽነሩ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ከሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት የህግ የማስከበሩ ስራ እንደሚቀጥልም ማረጋገጣቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img