Monday, October 14, 2024
spot_img

ባለሥልጣኑ የውጭ አገር ሚዲያዎች የትግራይን ጦርነት በሚዘግቡበት ወቅት ‹‹የትግራይ መከላከያ ኃይል›› ከማለት እንዲቆጠቡ አሳሰበ

አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ሐምሌ 10፣ 2013 ― የውጭ አገራት ሚዲያዎች ከትግራይ ክልል ጋር በተያያዘ በሚጠቀሙት አገላለጾች ዙሪያ ማሳሰቢያ እንደተሰጣቸው ተሰምቷል፡፡

የውጭ አገር ሚዲያዎች የትግራይን ጦርነት በሚዘግቡበት ወቅት ‹‹የትግራይ መከላከያ ኃይል›› ከማለት እንዲቆጠቡ የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን አሳስቧል።

የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ የሚሠሩ ዘገባዎችን ገምግሞም ሕወሓትን ብሔራዊ ሠራዊት እንዳለው በማድረግ የትግራይ መከላከያ ኃይል እያሉ የሚጠሩ አንዳንድ የውጭ ሚዲያዎች አሉ ብሏል።

በመግለጫውም ላይ እንደተጠቀሰው የትግራይ ክልል ከኢትዮጵያ ፌዴሬሽን አንዷ አካል ናት ካለ በኋላም የመከላከያ ኃይል ሊኖራትም አይችልም ብሏል።

ከዚህም በተጨማሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕወሓትን ሽብርተኛ ብሎ ከመሰየሙ ጋር ተያይዞ እንዲህ አይነት ስያሜዎችን መጠቀም የአገሪቱን የግዛት አንድነት፣ ብሔራዊ ጥቅምና ደኅንነት የሚጥስ ነው ብሏል።

በሌላ በኩል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኅዳር ወር በሕገ መንግሥታዊ መሰረት የትግራይ ክልል መንግሥትን አፍርሶ ጊዜያዊ አስተዳደር መስርቷል ተብሏል።

በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ ሪፖርቶችም ላይ እንዲሁ የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ተብሎ የሚጠቀስ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ቀኑን እስኪያስታውቅ ድረስ የተጠቀሰው የትግራይ መንግሥት የለም ብሏል። እስከዚያው ድረስ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እየመራ ይቆያል ብሏል መግለጫው።

የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን እንዲህ አይነት ቃላቶችን ከመጠቀም እንዲቆጠቡ ያሳሰበ ሲሆን እነዚህን ቃላቶች መጠቀም ማለት የኢትዮጵያን ሕግ የሚጥስና ጥብቅ እርምጃም የሚወስድ መሆኑን አሳስቧል።

ይህ ማሳሰቢያ የወጣው በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚዘጋጀውን አዲስ ስታንዳርድን የድረ ገጽ ሚዲያ ፍቃድ በጊዜያዊነት ማገዱን የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ካሳወቀ ከአንድ ቀን በኋላ መሆኑን የዘገበው ቢቢሲ ነው፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img