Sunday, October 6, 2024
spot_img

የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን አዲስ ስታንዳርድን ያገድኩት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተላለፈ ውሣኔ ባለማክበሩ ነው አለ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ሐምሌ 9፣ 2013 ― በትላንትናው እለት ፍቃዴ በመነጠቁ ሥራ አቁሜለሁ ያለው አዲስ ስታንዳርድን በተመለከተ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ምላሽ ሰጥቷል፡፡

ባለሥልጣኑ በበይነ መረብ ሚዲያነት የተመዘገበው አዲስ ስታንዳርድን ያገድኩት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተላለፈ ውሣኔን ባለማክበር አንድን የሽብር ቡድን ‹የመከላከያ ኃይል› ብሎ እውቅና እስከመስጠት በደረሰ ሁኔታ የሽብር ቡድኑ አጀንዳ ማራመጃ መድረክ መሆኑን›› ስላወቅሁ ነው ብሏል፡፡

የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣኑ ከዚህ በተጨማሪ አዲስ ስታንዳርድን አስመልክቶ ቅሬታዎች እንደደረሱት እእዲሁም ‹ራሱም ባደረገው ክትትል ‹‹አሳሳቢ አካሄድ›› ማስተዋሉን አመልክቷል፡፡

ባለሥልጣኑ በሚዲያው ላይ ያነሳቸውን ጉዳዮች እና ‹‹ሌሎችም ተያያዥ የሥነ ምግባር ግድፈቶች ላይ ጥልቅ ምርመራ›› እንደሚያደርግ እንዲሁም፣ ‹‹ሌሎች እርምጃዎችም›› ሊከተሉ እንደሚችሉ ጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ‹‹ለፕረስ ነጻነትና ሙያዊና በሥነ ምግባር የሚገዛ ጋዜጠኛነትን ለማበረታታት ያለውን ቁርጠኛነት በድጋሚ እንደሚያረጋግጥ›› በገለፀበት በዚሁ መግለጫው፣ ‹‹ነፃነት የሚመጣው ከኃላፊነትና ከተጠያቂነት ጋር መሆኑንም በተቆጣጣሪ አካልነቱ አጉልቶ ማስገንዘብ እንደሚፈልግ›› አመክልቷል።

አክሎም ሁሉም መገናኛ ብዙኃን የሕግ የበላይነትን እንዲያከብሩና በኃላፊነት ስሜት እንዲሠሩ አሳስቧል።

በጃኬን አሳታሚ ባለቤትነት ከ2003 አንስቶ በመጀመሪያ በመጽሔት ኅትመት፣ ከዚያም ከ2008 ወዲህ ደግሞ በበይነ መረብ ተወስኖ በእንግሊዝ አፍ መረጃዎችን የሚያቀርበው አዲስ ስታንዳርድ፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ከጥቂት ወራት በፊት ያወጣውን ማሳሰቢያ ተከትሎ በግንቦት ወር 2013 በድጋሚ የተመዘገበ ነው፡፡

የአዲስ ስታንዳርድን እግድ ተከትሎ ከሠሃራ በታች ተወካዩ በሆኑት ሙቶኪ ሙሞ በኩል መግለጫ ያወጣው የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ ሲፒጄ፣ የመንግሥትን ድርጊት ኮንኖ በአስቸኳይ የሚዲያው ፍቃድ እንዲመለስ ጠይቋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img