አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ሐምሌ 8፣ 2013 ― የፌዴራል መንግሥት በዛሬው እለት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሑሴን በኩል በሰጠው መግለጫ በትግራይ ክልል በእርዳታ ሰበብ እናስታጥቃለን የሚሉ ዓለም አቀፍ አካላትን ከአገር እንደሚያባርር አስታውቋል፡፡
በመግለጫው ላይ ከዚህ ቀደም በአገሪቱ በእርዳታ ሰበብ የሚያስታጥቁ መኖሩን ያስታወሱት አምባሳደር ሬድዋን፣ ከዚሁ ጋር በተገናኘ የተባበሩት መንግሥታትን ጨምሮ ሌሎችም የሰብአዊ እርዳታ ማድረስ ላይ ብቻ እንዲሠሩ አሳስበው፣ ካልሆነ ግን ከአገር እናስወጣለን ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል በዛሬው መግለጫ አንዳንድ የአውሮፓ አገራት ባለሥልጣናት እንዲሁም የምእራብ ዓለም ግለሰብ ባለሥልጣናት የትግራይን ጉዳይ የግላቸው አድርገው መውሰዳቸውና ለአንድ ወገን ያደላ አቋም ማንጸባቃቸውን አምባሳደር ሬድዋን ሑሴን ተናግረዋል፡፡
እነዚህ ግለሰቦች አቋማቸውን በቋሚነት በማስተጋባት ኢትዮጵያን የማዋከብ እና የማጨናነቅ ሁኔታ መፍጠራቸውን ያነሱት አምባሳደሩ፣ ጉዳዩ አስተዛዛቢ ሆኖ መቀጠሉን አመልክተዋል፡፡
ከዚሁ ጋር በተገናኘ ከሰሞኑ በአውሮፓ ኅብረት የተመድ የመብቶች ኮሚሽን ጥያቄ ባላቀረበበት ሁኔታ የውሳኔ ሐሳብ ማቅረቡን ኮንነው፣ ከባድ ድራማ በመስራት ተካሄዷል ባሉት ስብሰባ የውሳኔ ሐሳቡን ለተቃወሙትና ድምጸ ተአቅቦ ላደረጉ አገራት በመንግሥት ሥም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በአውሮፓ ኅብረት በኩል የተፈጸመውን ተገግባር የመንግሥትና አዎንታዊ እርምጃዎች የካደ ነው ብለውታል፡፡