አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ሐምሌ 8፣ 2013 ― በትግራይ ክልል በተነሳው ጦርነት አጣብቂኝ ውስጥ የገቡ ኤርትራውያን ስደተኞችን ደኅንነት ለመጠበቅ በመጠለያ ጣቢያዎች ፀጥታ የማስፈንና ወደተለያዩ አዳዲስ ጣቢያዎች የማዘዋወር ሥራ እየተሰራ መሆኑን የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ አስታውቋል፡፡
በዚህም መሰረት በማይ አይኒ እና አዲ ሐሩሽ የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙ ስደተኞች መደበኛ አገልግሎት ተጀምሯል የተባለ ሲሆን፣ በነዚህ የመጠለያ ጣቢያዎች 9 ሺሕ ያህል ስደተኞች የሰብዓዊ አገልግሎት እርዳታ እንዳገኙም በመግለጫው ሰፍሯል።
በትግራይ ክልል ተበታትነው የሚገኙ እና አዲስ አበባን ጨምሮ በመላው አገሪቱ ወደሚገኙ ከተሞች የፈለሱ ስደተኞች ምዝገባም እየተከናወነ እንደሆነም ተገልጿል።
እንደ ኤጀንሲው ከሆነ በአዲስ አበባ ብቻ ከ5 ሺሕ 200 በላይ ስደተኞች የተመዘገቡ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም ምዝገባው ቀጥሏል።
ከዚህም በተጨማሪ ኤጀንሲው ቁጥሩን በትክክል ባያስቀምጥም በርካታ ስደተኞች ወደ አፋር ክልል በራህሌ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ለማዘዋወር እንደተቻለም ተጠቅሷል፡፡
የተመድ ስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ ከሰሞኑ በኤርትራውያን ስደተኞች ላይ በጣም ከባድ የሆኑ የጥቃት ክሶች ሪፖርቶችን ሰምተናል በማለት፣ የፌደራል መንግሥትም ሆነ የትግራይ ክልል በእነዚህ ተዓማኒ ክሶች ላይ መደበኛ ምርመራ እንዲጀምሩ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በማይ ዓይኒ እና በአዲ ሐሩሽ መጠለያ ጣቢያች የሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች ደኅንነታቸው አደጋ ላይ ወድቋል ብለው በማሰባቸው ጥበቃ ወዳለበት አካባቢዎች እንዲዛወሩ ጠይቀዋል መባሉን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በድጋፍ ላይ የተመሰረተ የከተማ ስደተኝነት እውቅና እንዲሰጣቸው እና ወደ ሦስተኛ አገር እንዲዛወሩ ጥያቄ እያቀረቡ መሆኑ ነው የተነገረው፡፡
መንግሥትም ለዚህ ምላሽ ለመስጠት ከተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽን ጋር እየሰራ ነው ተብሏል።