Sunday, September 22, 2024
spot_img

የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ፊት ነስተዋቸዋል የተባሉት የአውሮፓ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ወደ አዲስ አበባ ሳይመጡ መቅረታቸው ተሰማ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ሐምሌ 8፣ 2013 ― ወደ አፍሪካ ቀንድ አገራት ባደረጉት የመጀመሪያ ጉዞ ከሁለት ቀናት በፊት ሱዳን ደርሰው ከአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብዳላ ሐምዶክ ጋር መገናኘታቸው የተነገረው የአውሮፓ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አኒት ዌበር፣ የአዲስ አበባ ጉዟቸውን መሰረዛቸውን የሚያመለክት መረጃ ወጥቷል፡፡

የአውሮፓ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛዋ የጉዞ ለውጥ ያደረጉት የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ፊት ስለነሷቸው መሆኑን አፍሪካን ኢንተሊጀንስ የተሰኘ ድረ ገጽ አስነብቧል፡፡

በጉዳዩ ላይ በይፋ የተነገረ ነገር ባይኖርም፣ የአውሮፓ ኅብረት በትግራይ ክልል ጉዳይ የሚያንጸባርቀው አቋም በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል እንዳልተወደደ የሚያመለክቱ ሁኔታዎች ተከስተዋል፡፡

ከነዚህ መካከል የሆነውና ከሁለት ቀናት በፊት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የመብቶች ጉባኤ በአውሮፓ ኅብረት ተወካይ አቅራቢነት ወደ ጠረጴዛው የመጣው በትግራይ ክልል ግጭት ያባብሳሉ የተባሉት የኤርትራ ወታደሮች የኢትዮጵያን መሬት ለቀው እንዲወጡ የሚጠይቀው የውሳኔ ሐሳብ አንደኛው ነው፡፡

በአውሮፓ ኅብረት የቀረበው የውሳኔው ሐሳብ ድጋፍ ማግኘቱን ተከትሎ፣ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ወቅቱን ያልጠበቀ ነው ያለውን ውሳኔ የተቃወመ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ከመንግሥታቱ ድርጅት የመብቶች ጉባኤ ጋር የሚያደርጉትንና በነሐሴ ወር ይፋ ይደረጋል በተባለው የትግራይ ክልል የሰብአዊ መብቶች ምርመራን የሚያሳንስ መሆኑንም ገልጾ ነበር፡፡

በሌላ በኩል በብራሰልስ የተሰበሰበው የአውሮፓ ኅብረት፣ በውጭ እና የደኅንነት ጉዳይ ኃላፊው ጆሴፍ ቦሬል በኩል የኅብረቱ አባል አገራት በትግራይ ክልል ባለው ቀውስ ምክንያት በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ ለመጣል እንዲያስቡ መጠየቁም ተሰምቶ ነበር፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img