Sunday, October 6, 2024
spot_img

ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ሕዝቡ ከመከላከያ ሠራዊት ጎን እንዲቆም ጥሪ አቀረቡ

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ሐምሌ 7፣ 2013 ― ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ባስነበቡት መግለጫ ሕዝቡ ‹‹እንደ አንድ ሠራዊት ሆኖ ለሀገሩ ሕልውና በመቆም፣ የመከላከያ ሠራዊቱን በሁሉም ነገር በመደገፍ፣ የውጪውን ጫና እና የውስጡን ትንኮሳ እንዲመክትና እንዲቀለብስ›› ጥሪ አድርገዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት ቀናት ‹‹ለትግራይ ሕዝብ ያለንን ሐሳብ፤ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ያለንን ቦታ ለመጨረሻ ጊዜ አሳይተናል›› ያሉ ሲሆን፣ ‹‹ግጭት ላለማባባስ፣ ለሕዝቡ የእርሻ ወቅት ፋታ ለመስጠት እንዲሁም የርዳታ አቅርቦቱ ያለ ሰበብ እንዲከናወን›› በሚል መንግሥት እድል መስጠቱን አስታውሰዋል፡፡

ሆኖም ሕወሃት ‹‹የሰላም መንገድ ሊዋጥለት አልቻለም›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሕወሃት ‹‹አሁን ባለው ቁመናው ያለ ግጭት ውሎ ማደር አይችልም፤ ሕጻናትና ወጣቶችን በአደንዛዥ ዕጽ እያሳበደ ወደ ጦርነት እየማገደ›› እንደሚገኝና ‹‹የመከላከያ ሠራዊቱ እነዚህን ሕጻናት ወታደሮች የመታደግ ሞራላዊ ግዴታ ወድቆበታል›› ብለዋል፡፡

አክለውም ለሕዝባችን ስንል የከፈልነው ዋጋ ባልገባቸው ደካሞች ምክንያት ውጤት አላመጣም ያሉ ሲሆን፣ ሕወሃትም ‹‹የኢትዮጵያ ህልውና ቀንደኛ ጠላት መሆኑን ደግሞ እያስመሰከረ››> መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

‹‹ይሄንንም መላ ሕዝባችንን አስተባብረን እንቀለብሰዋለን›› ያሉት ዶክተር ዐቢይ፣ ‹‹በአንድ በኩል ሰብአዊ ርዳታ እንዲቀላጠፍ እየሠራን፣ በሌላ በኩል የውጭና የውስጥ ጠላቶች ተናበው የከፈቱብንን ጥቃት መክተን እንቀለብሰዋለን›› ማለታቸው ተመላክቷል፡፡

በሌላ በኩል ሕወሃት ‹‹ዋሻ ውስጥ ገብቶ ሕዝቡ በረሐብ ሊያልቅ ነው እያለ ሲያላዝን ነበር›› ያሉ ሲሆን፣ ‹‹ለሕዝቡ ሲባል ሰብአዊ የተኩስ አቁም ሲደረግ ደግሞ የረሐቡን አጀንዳ ትቶ የጦርነት ነጋሪት መጎሰም›› መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

አያይዘውም ‹‹ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስለ ርዳታና ስለ ረሐብ ሲናገር መቆየቱን ዘንግቶ ሕወሃት ሕጻናትን ሲያሰልፍ እንኳን ዝምታን›› መምረጡን በመግለጽ፣ ‹‹የርዳታ መግቢያ ኮሪደሮችን የግጭት ቦታዎች ሲያደርጋቸው የርዳታ ድርጅቶች አሁንም መንግሥትን ለመውቀስ ይቃጣቸዋል›› ብለዋል፡፡ ነገር ግን ‹‹እነዚህን ሁሉ ከግምት በማስገባት መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ ነገር በተገቢው መንገድ›› እንደሚያደርግ ጠቁመዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመገለጫቸው ‹‹ሕዝባችን ከሐሰተኛ መረጃዎች እና ከጠላት ፕሮፓጋንዳ ራሱን እንዲጠብቅ›› ያሳሰቡ ሲሆን፣ ሕወሃትና አጋሮቹ ‹‹ያላቸው ዐቅም ውሸትን መፈብረክ ብቻ›› መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

በማሳረጊያቸውም ‹‹የውስጥና የውጭ ኃይሎች ፕሮፓጋንዳቸውን አቀናጅተው ሕዝብን ለመከፋፈል እየሠሩ›› እንደሆነ እንዲሁም ‹‹ለዚህ ደግሞ ሕዝባችን እንደ ከዚህ በፊቱ ሁሉ እንደ አንድ ሠራዊት ሆኖ ለሀገሩ ህልውና በመቆም፣ የመከላከያ ሠራዊቱን በሁሉም ነገር በመደገፍ፣ የውጪውን ጫና እና የውስጡን ትንኮሳ እንዲመክትና እንዲቀለብስ›› በማለት ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img