Sunday, September 22, 2024
spot_img

የአማራ ክልል በትግራይ አዋሳኝ አካባቢዎች በሕወሓት መጠነ ሰፊ ወረራ ተፈጽሞብኛል አለ

አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ሐምሌ 6፣ 2013 ― የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ባወጣው የሕወሃት ቡድን ትግራይን ከአማራ ክልል ጋር በሚያዋስኑት ሁሉም አቅጣጫዎች መጠነ ሰፊ ወረራና ጥቃት እየፈጸመብኝ ይገኛል ብሏል።

የክልሉ መንግስት አንድነታችንን ጠብቀን ያጋጠመንን የህልውና አደጋ በትግላችን እንቀለብሰዋለን ባለበት መግለጫው፣ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት በአንድ ወገን የወሰደውን የተኩስ አቁም ውሳኔ እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም በኢትዮጵያና በአማራ ክልል ህዝብ ላይ መሰረተ ሰፊ የሆነ ወረራና ጥቃት ማድረግ መጀመሩን ነው ያሳወቀው።

ቡድኑ የጀመረውን “ወረራ ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ እንደሚያወግዘውና የምንጊዜም አጋርነቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ፍጹም ጥርጣሬ የለንም፡” የአማራ ክልል፣ የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ “በግልጽ እንደሚያውቀው” በማለት “የአማራ ክልልና ሕዝብ የዚህ አሸባሪ ቡድን ቀጥተኛና የቅርብ ተጠቂ” መሆኑን አመልክቷል።

ስለሆነም ትግሉ “ለህዝባችን ህልውናና ለሀገር ሉአላዊነት መሆኑ ግንዛቤ ውስጥ ገብቶ የጋራ ጠላታችንን በጋራ እንድንፋለመው የአጋርነት ጥሪያችንን እናቀርባለን፡” ብሏል።

የክሉ መንግስት በመግለጫው ሕወሃት “የትግራይን ህዝብ ከህጻን እስከአዋቂ በማንቀሳቀስ አለም አቀፍ የጦርነት ህግጋትን በመቃረን ህጻናትንና ሴቶችን በጅምላ ጦርነት እየማገደና ያለ የሌለውን አቅሙን ተጠቅሞ” በክልሉ ላይ ወረራ ፈጽሟል ያለ ሲሆን፣ “በተለይም ለዘመናት የአማራ ህዝብ የማንነትና የወሰን ጥያቄ እያነሳ ሲታገልባቸው የቆዩ የራያ አላማጣና ኮረም አካባቢዎችን ዳግም በመውረር እንዲሁም ወልቃይት ጠገዴ ሴቲት ሁመራ በኃይል ለመያዝ በተለይም ጠለምትና አካባቢውን ለመያዝ አሁናዊ ሙከራ የጀመረ መሆኑ በአካባቢው የሚኖሩ አማራዎችንና የአማራ ክልል ተወላጆችን ፈጽሞ የማጥፋት ህልሙን እውን ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ” ይገኛልም ሲል አመልክቷል።

ስለሆነም ይህን በአማራ ክልል መንግስት አረመኔያዊ የተባለውን ድርጊት ያወገዘው መግለጫው፣ “የክልሉ መንግስት በፍጹም የማይቀበለውና በጀመርነው የህልውና ትግል ተፈጥሯዊና ታሪካዊ መብታችንን የምናረጋግጥ መሆኑን” እወቁልኝ ነው ያለው።

ለዚህም በየግንባሩ የሚገኙ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት፣ የክልሉ ልዩ ኃይልና የሚሊሻ አባላት፣ ህዝባዊ ፖሊስና ሰላም አስከባሪ አባላት እንዲሁም “አገርና ህዝብን ለማዳን” የተግባር እንቅስቃሴ እያደረጋጉ ነው ያላቸውን የየክልሉ የጸጥታ አካላት “በዚህ ታሪካዊ መድረክ ከጠላት ጋር ፊት ለፊት በመግጠም ለአገራችሁ ሉአላዊነትና ለህዝባችሁ ህልውና የምትከፍሉትን ክቡር መስዋዕትነት ታሪክ ምንጊዜም ሲያስታውሰው” እንደሚኖር ገልጿል።

እነዚህን የጸጥታ አካላት “መላው የኢትዮጵያና የአማራ ህዝብ ከጎናችሁ መሆኑን አውቃችሁ በጀግንነት ታሪካዊ ጠላታችንን በመደምሰስ ለአገራችሁ ዳግም የኩራት ምንጭ እንድትሆኑ” በማለት ጥሪውን አቅርቧል።

በተጨማሪም “መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በትህነግ ወያኔ ላይ የተጀመረው ህግን የማስከበር ትግል ተጠናክሮ እንዲቀጥል አስፈላጊውን ርብርብ ሁሉ ማድረግ አለበት” ብሏል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img