Sunday, September 22, 2024
spot_img

የአማራ ክልል መንግሥት በትግራይ እርዳታ ጉዳይ አላግባብ ሥሜ እየጠፋ ነው አለ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ሐምሌ 5፣ 2013 ― የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አንዳንድ የውጭ ሚዲያዎችና የማኅበረሰብ አንቂዎች የአማራ ክልል መንግሥት ወደ ትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ እንዳይገባ እያደረገ ነው በሚል የሚያሰራጩት ዘገባ ፍጹም የክልሉን መንግሥትም ሆነ ሕዝብ የማይወክልነው ሲል መግለጫ አውጥቷል፡፡

የክልሉ መንግሥት በመግለጫው የሰብዓዊ እርዳታ የሚያቀርቡ ድርጅቶችም ሆነ ሀገራት በሰብዓዊ እርዳታ ስም ያልተፈቀደላቸውንና ህገ ወጥ የሆኑ ቁሳቁሶች ለአብነትም የጦር መሳሪያ፣ አደንዛዥ እፆች፣ አውዳሚ ኬሚካሎች እና የመሳሰሉት ጠቃሚ ያልሆኑና ለማኅበረሰባችን የበለጠ ቀውስ ሊፈጥሩ የሚችሉ ቁሶች በአሸባሪነት ለተፈረጀው የሕወሓት ኃይል እንዳይደርስ ስጋት ስላለብኝ እከላከላለሁ ብሏል፡፡

ለዚህም የክልሉ መንግሥት የዜጎቹን ደኅንነት የመጠበቅ ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ በእርዳታ ስም የሚጓጓዘው አልሚ ምግብ፣ እህል ወይም ሌላ ቁስ በእርግጥም ትክክለኛ የሰብዓዊ እርዳታ ስለመሆኑ ማረጋገጥ ይፈልጋል ነው ያለው።

ስለሆነም የክልሉ መንግሥት ከፌዴራል መንግሥት ጋር በጋራና በምክክር እየሠራ ያለው ነገር ቢኖር አማራ ክልልን አልፎ የሚሄድ የትኛውም የእርዳታም ይሁን የንግድ ሸቀጥ በፍተሻ ኬላዎች እየተፈተሸ ሕጋዊና የተፈቀደ የሰብዓዊ እርዳታ ቁስ መሆኑን በማረጋገጥ ብቻ ነው ያለ ሲሆን፣ ከዚህ ውጭ ሰብዓዊ እርዳታው እንዳይደርስ የማስተጓጎል ፍላጎት የለውም ብሏል።

ከፍተሻ በመለስ ትክክለኛው የሰብዓዊ እርዳታ ከሆነ እንድያውም ደኅንነቱ ተጠብቆ እንዲደርስ በክልሉ ውስጥ እርዳታ ጭነው የሚመጡ አካላትንም ሆነ የሚጓጓዘውን እርዳታ ደኅንነቱ ተጠብቆ እንዲደርስ እያደረገ እንደሚገኝና ለወደፊቱም የሚያደርገው ይሄንኑ መሆኑ መታወቅ እንዳለበት ገልጿል።

ከዚህ ውጭ የክልሉ መንግሥት ለምን ፍተሻ ያደርጋል በሚል በውጭ ሚዲያዎችና በማኅበረሰብ አንቂዎች በተዛባ መንገድ የአማራ መንግሥት የሰብዓዊ እርዳታ ወደ ትግራይ ክልል እንዳይገባና እርዳታ ለሚያስፈልገው የኅብረተሰብ ክፍል እንዳይደርስ እያደረገ ነው የሚለው ክስ ምናልባትም “ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ጅግራ ናት ይሏታል እንደሚባለው” ሳይሆን አይቀርም ብሎታል፡፡

‹‹በተዛባው የውጭ ሚዲያና በሕወሓት ቅጥረኛ የማኅበራዊ ሚዲያ የሐሰት ክስ መንግሥት መደበኛ የደኅንነት ሥራውን የማያቆም›› መሆኑንም የክልሉ መንግሥት እንዲታወቅልኝ ይሁን ብሏል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img