Monday, October 14, 2024
spot_img

ወደ ትግራይ ክልል የሚላከው የደም አቅርቦት መቋረጡ ተነገረ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ሐምሌ 5፣ 2013 ― የብሔራዊ ደም ባንክ አገልግሎት ወደ ትግራይ ክልል የሚልከው የደም አቅርቦት መቋረጡን አስታውቋል፡፡

እንደ ባንኩ ከሆነ ለደም አቅርቦት ሂደቱ እንቅፋት የፈጠረው ወደ ክልሉ የሚሄድ የትኛውም ዐይነት የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ባለመኖሩ ነው፡፡

የብሔራዊ ደም ባንክ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ያረጋል ባንቴ እንደገለጹት፣ ሌሎች አከባቢዎች ላይ የደም አቅርቦቱ በተሳካ ሁኔታ እየሄደ ቢሆንም፣ ለትግራይ ክልል ይቀርብ የነበረው የደም አቅርቦት ግን ተቋርጧል።

የአገር መከላከያ ሠራዊት ክልሉን ለቆ ከመውጣቱ አስቀድሞ መቐለ በሚገኘው የደም ባንክ ለሁለት ዓመት ያክል የሚያገለግል የደም ክምችት ባንኩ ማቅረቡን የገለጹት ያረጋል፣ ነገር ግን አክሱም ላይ እጥረት ሊያጋጥም ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን አጋርተዋል፡፡

ይሁን እንጂ በተቀሩት የክልሉ አከባቢዎች ላይ ያን ያክል የሚያሰጋ የደም አቅርቦት ችግር ላይኖር እንደሚችል ዳይሬክተሩ አስረድተዋል። በክልሉ ውስጥ ባሉ የጤና ተቋማት በሕክምና ላይ ላሉ ሕሙማን እንዲሁም ለወደፊት ግጭት ከተከሰተ ተጨማሪ የደም አቅርቦት ስለሚያስፈልግ ዜጎች በበጎ ፍቃደኝነት ደም እንዲለግሱ የማድረግ ሥራ መሠራት አለበት ብለዋል።

በግጭቶች እና ጦርነቶች ጉዳት የሚደርስበት ሰው ከበዛ ፍላጎቱ ስለሚጨምር አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ይፈጥራል ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ይህ ከሆነም በኢትዮጵያ የማይመከር ቢሆንም የመጨረሻ አማራጭ የሚሆነው የቤተሰብ ምትክ ደም ፈልጎ መጠቀም እንደሆነም ጨምረው ተናግረዋል።

ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት ባለሙያዎች ወደ ትግራይ ክልል እንዳይሄዱ የተደረገ ሲሆን፣ ችግሩ ረዥም ጊዜ የሚዘልቅ ከሆነ አሳሳቢ እንደሚሆን ገልፀዋል። የመንግስትን አቅጣጫ በመከተል ወደፊት የሚሻሻሉ ነገሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቁመዋል መባሉንም የዘገበው አዲስ ማለዳ ጋዜጣ ነው፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img