አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ሐምሌ 5፣ 2013 ― ከቱጃሩ ሼይኽ መሐመድ አሊ አል አሙዲ ንብረቶች መካከል የሆነው ሚድሮክ ፋውንዴሽን የሚጠበቅበትን ዕዳ ባለመክፈሉ ንብረቶቹ በሐራጅ ሊሸጡ መሆኑ ተነግሯል፡፡
የፋውንዴሽኑ ንብረቶች ይሸጣሉ የተባለው፣ ከቀድሞ ሸሪኩ አኪን ብራኡን ባለቤትነት ለሚተዳደረው ሜዲትራንያን ከተሰኘ ድርጅት ለተከራየው የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች ክፍያ አልከፍልም በማለቱ እሰጣ ገባ ውስጥ ገብቶ ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት አምርቶ ነው፡፡
አኪን የሚድሮክ ፋውንዴሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ እና ባለድርሻ በነበረበት ጊዜ በሥሙ ለተከፈተ ሜዲትራንያን ለተሰኘ ኩባንያ የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎችን ማከራየቱን በመግለፅ፣ ሚድሮክ ክፍያውን መፈፀም የለብኝም በሚል ተከራክሮ ነበር ነው የተባለው፡፡
ጉዳዩን የተመለከተው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሚድሮክ ፋውንዴሽን ያቀረበውን መከራከሪያ ውድቅ በማድረግ፣ የሚጠበቅበትን 21 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ለድርጅቱ እንዲከፍል አልያም ንብረቶቹ በሐራጅ ተሽጠው ዕዳውን እንዲከፍል ወስኗል።
ሚድሮክ ፋውንዴሽን ውሳኔውው በመቃወም ለሰበር ፍርድ ቤት ይግባኝ ቢልም፣ ይግባኙ ውድቅ እንደተደረገበት ፎርቹን ጋዜጣ ዘግቧል፡፡