Sunday, September 22, 2024
spot_img

ኢትዮጵያ ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የኮቪድ ክትባት ልትገዛ መሆኑ ተሰማ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ሐምሌ 2፣ 2013 ― ኢትዮጵያ ከዓለም ባንክ የኮቪድ 19 ማገገሚያ ያገኘችውን ወደ 207 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ድጋፍ ለክትባት ግዥ ልታውለው እንቅስቃሴ መጀመሯን ዋዜማ ራድዮ ዘግቧል፡፡

በዚህም መሰረት ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ከተሰኘው ከታዋቂው የአሜሪካ የመድሃኒት አምራች ኩባንያ የኮቪድ 19 ክትባት ለመግዛት ውል እንደፈፀመችም ተነግሯል።

ኢትዮጵያ የጆንሰን ኤንድ ጆንሰን የኮቪድ 19 ክትባትን ለመግዛት የፈፀመችው ውል 3 ሚሊዮን ለሚጠጋ የክትባት ጠብታ ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪም ወደ 4 ሚሊዮን የሚጠጋ የአስትራ ዜኒካ ክትባትንም በግዥ ለማስገባት አስፈላጊው ሁሉ እንደተፈፀመ ነው የተሰማው፡፡

ኢትዮጵያ ኮቫክስ ከተሰኘው የኮቪድ 19 ክትባትን ለታዳጊ ሀገራት ለማዳረስ በተቋቋመው ጥምረት አማካኝነት በዚሁ አመት መጋቢት ወር ላይ ወደ 2 ነጥብ 2 ሚሊየን ጠብታ የአስትራዜኒካ ክትባት ተረክባ የመጀመሪያ ዙር ክትባት ስታዳርስ መቆየቷ ይታወቃል።

ሁለተኛውን ዙር ክትባት ለማዳረስ የሚያስችል የአስትራዜኒካ ክትባት በተለይ 391 ሺሕ የአስትራዜኒካ ክትባትን ሀገሪቱ በጥቂት ቀናት ውስጥ ከኮቫክስ ጥምረት ትረከባለች ተብሎ እየተጠበቀ መሆኑን ዘገባው አመልክቷል፡፡ ክትባቱ ምናልባትም በቀጣዮቹ አምስት ቀናት ኢትዮጵያ እንደሚገባም ይጠበቃል ነው የተባለው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ከነሐሴ እስከ መስከረም ወር ድረስ 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ጠብታ የአስትራ ዜኒካ ክትባትን ለመረከብ እየተዘጋጀች የምትገኘው ኢትዮጵያ ሰሞኑን ከሚገባው ወደ 400 ሺሕ ጠብታ ከሚጠጋው ክትባት ጋር በድምሩ ወደ 2 ነጥብ 2 ሚሊየን ጠብታ ክትባትን እንደምታገኝ ይጠበቃል።

ይህ ደግሞ በመጀመሪያው ዙር የአስተራ ዜኒካ ክትባት የከተበቻቸውን እና አዲስ የሚከተቡ ዜጎቿን በሙሉ ሁለተኛ ዙር የአስትራ ዜኒካ ክትባት ለማዳረስ እንደሚያስችላትም መነገሩን ዘገባው አክሏል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img