Sunday, October 6, 2024
spot_img

የፀጥታው ምክር ቤት የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ድርድር በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት መቀጠሉን ደገፈ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ሐምሌ 2፣ 2013 ― ትላንት ምሽት በተካሄደው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባ በሕዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር ዙሪያ ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳንን ጨምሮ አባል አገራቱ መክረዋል።

በዚሁ ስበሰባ ላይ ኢትዮጵያ ድርድሩ በአፍሪካ ኅብረት በኩል እንዲቀጥል አጥብቃ ጠይቃለች። ይኸው ድርድሩ በአፍሪካ ኅብረት ይደረግ የሚል ሐሳብ አሜሪካን ጨምሮ በጎረቤት ኬንያ፣ ሩሲያ፣ እንግሊዝ እና ህንድ ድጋፍ አግኝቷል፡፡

በስብሰባው ኢትዮጵያን ከወከሉት መካከል የሆኑት የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ስለሺ በቀለ፣ የሕዳሴው ግድብ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ያለውን ቦታ ያነሱ ሲሆን፣ ምክር ቤቱ ጉዳዩን ወደ አፍሪካ ኅብረት እንዲመልሰው አጥብቀው ጠይቀዋል፡፡

ዶክተር ስለሺ በምክር ቤቱ ያደረጉትን ንግግር ጉዳዩ ወደ ጸጥታው ምክር ቤት መሄዱ እንዳሰዘናቸው በመግለጽ ጀምረዋል፡፡ የጸጥታው ምክር ቤት ጉዳዩ እንደማይመለከተውም አጽንኦት ሰጥተው አስረድተዋል፡፡

‹‹የሕዳሴው ግድብ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አሻራ የታተመበት ነው›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ ‹‹ግድቡ በደም እና በእንባ የተገነባ›› መሆኑንና ምክር ቤቱ የሚፈልገው ከውሃው እንዳንጠቀም ነው ወይ ሲሉ ጠንከር ያለ ጥያቄ ሰንዝረዋል፡፡

ዶክተር ስለሺ አክለውም ቀጠሉ የዓባይ ውሃ በበረሃ ለሚኳትነው ኢትዮጵያዊ ወገን ተስፋ መሆኑን፣ የተለያዩ እስር ቤቶችን ላጣበቡ ኢትዮጵያዊያንም ተስፋቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የውሃ ሙሌቱን በተመለከተም ሁለተኛው ዙር ሙሌት የግንባታው አንድ አካል እንደሆነ እንዲሁም፣ ኢትዮጵያ በግድቡ ግንባታ ሂደት አሁን ላይ በደረሰበት ሁኔታ መሞላቱ የሂደቱ አካል መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

ዶክተር ስለሺ በማሳረጊያቸው ለምክር ቤቱ አባላት ኢትትጵያን ከተደራዳሪ አገራት ጋር ለመዳኘት መሞከር ሌላ ችግር የሚያስከትል መሆኑን አንስተው፣ የጸጥታው ምክርቤት ወደ ፊት ይህን መሰል ነገሮች ሲቀርቡለት እየዳኘ ሊቀጥል ቢል የሚዘልቀው እንዳልሆነና ጉዳዩ አይመለከተኝም ብሎ ወደ አፍሪካ ኅረት ይምራው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

በዚሁ ስብሰባ ላይ ጉዳዩን ወደ አፍሪካ ኅብረት መወሰድ ከደገፉት መካከል የሆነችው ሩስያ በተወካዩዋ ቫሲሊ ኔቤንዝያ በኩል፣ በግድቡ ጉዳይ ‹‹ኃይል እጠቀማለሁ የሚል አካሄድ መወገድ አለበት፣ ፍጥጫ እና መካረር ያለውን ችግር ለመፍታት አያስችልም›› ብላለች፡፡

በሌላ በኩል የአየርላንድ ተወካይ ‹‹ዘላቂነት ያለው የውሃ አስተዳዳር ያሻል፡፡ ስለ ሙሌቱም ሆነ ስለ ሌላው ጉዳይ ለሱዳንም ለግብጽም መረጃ ክፍት መሆን አለበት›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

በስብሰባው ሐሳብ የሰነዘሩት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር ሊንዳ ቶምሰን ግሪንፊልድ በበኩላቸው በአፍሪካ ኅብረት በኩል የሚደረግን ሁሉንም ተደራዳሪዎች የሚጠቅም ድርድር እንዲረግ ጠይቀዋል፡፡

ከተለያዩ አገራት ተወካዮች ሐሳብ የተሰነዘረበት ምክር ቤቱ በግድቡ ጉዳይ የሦስቱን ሀገራት የጋራ ጥቅም ባከበረ መልኩ ድርድሩ በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት እንዲቀጥል ወስኗል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img