Wednesday, October 9, 2024
spot_img

በሐሰተኛ ማስረጃ የ20 ዓመት ፅኑ እስራት የተፈረደባቸው ግለሰብ ከእስር ነፃ ተለቀቁ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ሐምሌ 1፣ 2013 ― በሀሰተኛ ማስረጃ የ20 ዓመት ፅኑ እስራት የተፈረደባቸው ግለሰብ በልዮ ሁኔታ ያለ ቅድመ ሁኔታ ከእስር ነፃ መውጣታቸውን የአማራ ክልል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መስሪያ ቤት አስታወቀ።

የአማራ ክልል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መስሪያ ቤት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዓለምሸት ምህረቴ፣ በሰሜን ሸዋ ዞን ሞጃና ወደራ ወረዳ የሰላ ድንጋይ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ግለሰብ ከአምስት ዓመት በፊት በእንጀራ እናቷ ወይዘሮ አዛለች ቤተምንዳ ተገድላለች በሚል ግለሰቧ መሞቷ በሃሰተኛ ማስረጃ ተረጋግጦ ወይዘሮ አዛለች ቤተምንዳ የ20 ዓመት ፅኑ እስራት ቅጣት ተጥሎባቸው ነበር።

ወይዘሮ አዛለች ቤተምንዳ የእንጀራ ልጇን ገድላለች በሚል የሰሜን ሸዋ ዞን ዐቃቤ ሕግ የወንጀል መዝገብ ቁጥር 134/2008 ክስ መስርቶባቸው ሲከራከሩ መቆየታቸውን ተገልጿል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤትም የቀረበውን ክስና ማስረጃ በመመርመር ጥፋተኛ ናቸው ብሎ በ20 ዓመት ፅኑ እስራት እና በአምስት ዓመት ከማንኛውም ማህበራዊ ግንኙነት እንዲገለሉ ውሳኔ አስተላልፎ እንደነበር ገልጸዋል።

በተሠጠው ውሳኔ መሠረትም ወይዘሮ አዛለች ቤተምንዳ አምስት ዓመት በደብረብርሃን ማረሚያ ቤት በእስር መቆየታቸው ተገልጿል።

ነገር ግን ሞተች ተብላ በሀሰተኛ ማስረጃ የተረጋገጠላት ግለሰብ ከሌላ አካባቢ በሕይወት ቆይታ በቅርብ ጊዜ ወደ ትውልድ አካባቢዋ በመምጣቷ ሞተች ተብላ ጥፋተኛ ያልሆነችን ግለሰብ እንደ ጥፋተኛ ቆጥሮ ማረሚያ ቤት እንድትወርድ ያደረገችው ግለሰብ ማንነቷ በአካባቢው ህብረተሰብ እና በማስረጃ ተረጋግጧል ብለዋል።

በዚህም በሃሰተኛ ማስረጃ ተፈርዶባቸው በእስር የቆዩት ወይዘሮ አዛለች ቤተምንዳ በአማራ ክልል የተሻሻለው የይቅርታ አሰጣጥ መወሰኛ መመሪያ ቁጥር 30/2010 መሠረት ጉዳያቸው ለአማራ ክልል ይቅርታ ቦርድ ቀርቦ የክልሉ ምክር ቤት በ29 ቀን 2013ዓ.ም ባካሄደው 5ኛ ዙር 6ኛ ዓመት የስራ ዘመን 13ኛ አስቸኳይ ስብሰባ ወ/ሮ አዛለች ቤተምንዳ በልዮ ሁኔታ ያለ ቅድመ ሁኔታ ከእስር ነፃ እንዲወጡ እና የተጣለባቸው ገደብ እንዲነሳላቸው ወስኗል።

የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው በወይዘሮ አዛለች ቤተምንዳ ላይ የገጠመው ጉዳይ ያለ ማስረጃ የሚታሰሩ ታራሚዎች በሞራል፣በኢኮኖሚ፣በማሕበራዊ፣በ ቤተሰብ ላይ የሚደርስባቸውን ጉዳት ካሳ የሚካሱበት የሕግ ማዕቀፍ የሌሎች አገሮችን ልምድ በመቀመር ማዘጋጀት እንደሚገባ አስተማሪ ሆኖ አልፏል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img