Sunday, September 22, 2024
spot_img

በትግራይ በሰብዓዊ መብት ጥሰት የተጠረጠሩ የኢትዮጵያ ወታደሮች በሰላም አስከባሪነት ከማገልገል እንዲታገዱ ተጠየቀ

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ሰኔ 30፣ 2013 ― በትግራይ ክልል ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ የኢትዮጵያ ወታደሮች በተባበሩት መንግስታት የሰላም አስከባሪነት ከማገልገል እንዲታገዱ የአሜሪካ ሴኔት የውጭ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ ሊቀመንበር ሴናተር ቦብ ሜንዴዝ ጥሪ አቀረቡ። የቋሚ ኮሚቴው ሊቀመንበር ጥሪውን ያቀረቡት ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በጻፉት ደብዳቤ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንሳይደር ድረ ገጽ ዘገባ ያመለክታል፡፡

ዘጠነኛ ወሩን ሊደፍን በተቃረበው የትግራይ ግጭት፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት ከኤርትራ ወታደሮች እና ከሌሎችም የታጠቁ ሃይሎች ጋር በመሆን ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ስለመፈጸማቸው የሚሳዩ ማስረጃዎች አሉ ሲሉ ሊቀመንበሩ በደብዳቤያቸው ወንጅለዋል።

ሴናተሩ የኢትዮጵያ ወታደሮችን ከከሰሱባቸው ወንጀሎች መካካል በተደራጀ ሁኔታ የሚፈጸም አስገድዶ መድፈር፣ ሰላማዊ ሰዎችን ማስራብ፣ የዘፈቀድ ግድያዎች እና ጭፍጨፋዎች ይገኙበታል። ከዚህም በተጨማሪ ወታደሮቹ በጦር ወንጀል እና በሰብዓዊነት ላይ በተፈጸሙ ወንጀሎች ስር ሊመደቡ የሚችሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ፈጽመዋል ሲሉ ይከስሳሉ።

‹‹የኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ጨምሮ በዘግናኙ የትግራይ ግጭት ላይ የተሳተፉ ሁሉም ወገኖች በሺህዎች በሚቆጠሩ የትግራይ ሰላማዊ ሰዎች ላይ የጭካኔ ተግባር በመፈጸም ይወነጀላሉ›› ያሉት ሜንዴዝ፤ በእንደዚህ አይነት ወንጀሎች የሚጠረጠሩ ወታደሮች በተባበሩት መንግስታት ሰላም አስከባሪነት ለማገልገል ‹‹ብቁ አይደሉም›› ሲሉ በደብዳቤያቸው ላይ በአጽንኦት አሳስበዋል።

‹‹የኢትዮጵያ መንግስት ለተባበሩት መንግስታት የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች በርካታ ወታደሮች ከሚያዋጡት አንዱ እንደመሆኑ፤ የተባበሩት መንግስታት ደርጅት በሰላም ማስከብር ተልዕኮዎች ላይ የሚመደቡ የኢትዮጵያ ወታደሮች በትግራይ ወታደራዊ ዘመቻ ላይ ስለመሳተፋቸው ብርቱ የማጣራት ሂደት እንዲያከናውን እንጠይቃለን›› ሲሉ የአሜሪካ ሴኔት የውጭ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ ሊቀመንበር በደብዳቤያቸው ጥያቄ አቅርበዋል።

የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ በ1995 ባሳለፈው ውሳኔ፤ የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ በሰብዓዊ እና የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ላይ ወሲባዊ ብዝበዛ እና በደል እንዳይፈጸም ለመከላከል እርምጃዎች እንዲወስዱ ኃላፊነት እንደጣለባቸው ሜንዴዝ በደብዳቤያቸው አስታውሰዋል። የመንግስታቱ ድርጅት በ2003 ተግባራዊ ማድረግ የጀመረው የቅድመ ማጣራት ፖሊሲም፤ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ እና የሰብዓዊ መብቶች ህጎችን በከፍተኛ ሁኔታ በመጣስ የተጠረጠሩ ግለሰቦች በሰላም አስከባሪነት ከመመደብ እንዲታገዱ እንደሚያደርግ ጠቅሰዋል።

የመንግስት ኃይሎች እነዚህን መሰል የጭካኔ ተግባራት ለመፈጸማቸው ተጠያቂ በሚሆኑበት ወቅት፤ ለሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች የሚመደቡ የየሀገራቱ የፖሊስ እና ወታደራዊ ሰዎች፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከተለመደው የማጣሪያ ሂደት በመሻገር በጥብቅ የሚፈተሽበት አሰራር እንዳለው ሜንዴዝ በደብዳቤያቸው ጠቁመዋል። ከዚህ ቀደም በብሩንዲ እና ሲሪላንካ የመንግስት ኃይሎች ላይ የተካሄደውን መሰል የማጣራት ስራንም በምሳሌነት አንስተዋል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img