Sunday, October 13, 2024
spot_img

አሜሪካ የሕዳሴው ግድብ ሁለተኛ ዙር ሙሌት ውጥረትን የመጨመር አቅም አለው አለች

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ሰኔ 30፣ 2013 ― የሕዳሴውን ግድብ ሁለተኛ ዙር ሙሌት መጀመሩ፤ በኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ መካከል ‹‹ውጥረትን ከፍ የማድረግ አቅም አለው›› ስትል አሜሪካ አሳሰበች። ሀገሪቱ ሁሉም ወገኖች ውጥረትን ከሚያባብሱ የተናጠል እርምጃ እንዲታቀቡ ጥሪ አቅርባለች።

ይህን የአሜሪካ አቋም ትላንት ማክሰኞ ምሽት ይፋ ያደረጉት የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቃባይ ኔድ ፕራይስ ናቸው። ቃል አቃባዩ በዕለታዊ ጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ እንደተናገሩት፤ ሦስቱ ሀገራት በሕዳሴው ግድብ ላይ ዘላቂ የሆነ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ አሜሪካ ‹‹በትብብር መንፈስ የተሞላ እና ገንቢ›› ጥረት ማድረጓን ትቀጥላለች።

‹‹የአባይ ውሃ ለሶስቱ ሀገራት ያለውን ያለውን ዋጋ እንረዳለን›› ያሉት ቃል አቃባዩ፤ ሀገራቱ በህዳሴው ግድብ ላይ ያቋረጡትን ውይይት እንዲቀጥሉ ሀገራቸው ማበረታቷን እንደምትቀጥል ተናግረዋል።

ውይይቱ ‹‹ፍሬያማ፣ ተጨባጭ እና ገንቢ›› ይሆናል የሚል ተስፋም እንዳላቸውም ገልጸዋል። በዚህ እሳቤ ላይ በመመስረትም አሜሪካ በአፍሪካ ህብረት የሚመራውን ሂደት ስትደግፍ መቆየቷንም አክለዋል።

የአፍሪካ ህብረት መር ሂደቱ ‹‹ውጥረትን ለመቀነስ፣ ፍሬያማ ድርድሮችን ለማመቻቸት እና ቀጠናዊ ትብብሮችን ለማጎልበት›› ያለመ እንደሆነ በመግለጫቸው የጠቀሱት ፕራይስ፤ በሶስቱ ሀገራት የሚካሄድ የተናጠል እርምጃ ግን ከዚህ በተቃራኒው ‹‹ውጥረቶችን የሚጨምር ነው›› ሲሉ ተችተዋል። ማንኛውም የተናጠል እርምጃ አሁን ጉዳዩ ባለበት ደረጃ እና ሰላማዊና ገንቢ መፍትሄ ማምጣት በሚለው እቅድ መካከል ‹‹ትልቅ ክፍተት›› ይፈጥራል ሲሉም ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ያከናወነችው ሁለተኛ ዙር የሕዳሴው ግድብ የውሃ ሙሌት ‹‹እንደ ተናጠል እርምጃ›› ይቆጠር እንደው ከጋዜጠኛ ጥያቄ የቀረበላቸው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቃባይ፤ ድፍን ያለ መልስ በመስጠት በቀጥታ ምላሽ ከመስጠት ለመቆጠብ ሞክረዋል። ‹‹የውሃ ሙሌቱ ውጥረቶችን የሚጨምር የተናጠል እርምጃ ሊባል ይችላልን?›› የሚል ጥያቄ በድጋሚ የቀረበላቸው ቃል አቃባዩ፤ ለጥያቄው አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተዋል።

‹‹እንደማስበው ይህ ጉዳይ ውጥረቶችን ከፍ የማድረግ አቅም አለው ማለት አግባብ ነው›› ብለዋል ሲል የዘገበው ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ነው፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img