Sunday, September 22, 2024
spot_img

ጄኔራል ፃድቃን ገብረትንሳይ በድርድር ላይ የተመረኮዘ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን መናገራቸው ተሰማ

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ሰኔ 30፣ 2013 ― የሕወሃት ኃይሎችን እየመሩ እንደሆነ የሚነገርላቸው ጄኔራል ፃድቃን ገብረትንሳይ፣ ለትግራይ ጦርነት በድርድር ላይ የተመረኮዘ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ነግረውኛል ብሎ ሬውተርስ ዘግቧል፡፡

የዜና ወኪሉ አድርጌዋለሁ ባለው ቃለ ምልልስ ‹‹ለችግሩ ፖለቲካዊ መፍትሔ ለማግኘት እንሻለን፤ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይህን እንዲገነዘብ እፈልጋለሁ፤ አማራጭ ካጣን ግን በወታደራዊ ርምጃ ችግሩን እንፈታለን›› ማለታቸው ተመላክቷል፡፡

ጄነራሉ በይፋ ካልተገለጸ ሥፍራ ሆነው በሳተላይት ስልክ አድርገውታል በተባለው ቃለ ምልልስ፤ ለትግራይ ግጭት ፖለቲካዊ መፍትሔ እንደሚያስፈልግ መጠቆማቸው ነው የተዘገበው፡፡

የፌደራል መንግሥት ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ከትግራይ ክልል አካባቢዎች መከላከያ ሠራዊቱን አስወጥቶ፤ የተናጠል የተኩስ አቁም ማወጁ ይታወሳል።

ለተኩስ አቁሙ ምላሽ የሰጠው ሕወሃት፣ ስምምነቱን ለመቀበል ሰባት ቅድመ ሁኔታዎችን ማስቀመጡ መነገሩም አይዘነጋም፡፡

ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እንዲሁም አገራት የፌደራል መንግሥት የተኩስ አቁምን በአዎንታዊ መንገድ እንደሚያዩት ሲገልጹ የቆየ ሲሆን፣ ይህም ተኩስ አቁም ለግጭቱ ማብቂያ እንዲሆንም ጥሪ አቅርበዋል።

የመከላከያን ከክልሉ መልቀቅ መናገሩን ተከትሎ የሕወሃት ኃይሎች ሠራዊቱን ድል አድርገው መቀለን ጨምሮ ሌሎችም የትግራይ ከተሞችን በቁጥጥራቸው ሥር እንዳዋሉ ገልጸዋል፡፡

ጄኔራል ፃድቃን ከሬውተርስ የዜና ወኪል ጋር ባደረጉት ቆይታም፣ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ በትግራይ መሸነፋቸውን ካላመኑ ጦርነቱ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

አያይዘውም መንግሥት ሰብዓዊ ርዳታ ወደ ክልሉ እንዳይደርስ ሆነ ብሎ እያስተጓጎለ መሆኑን መናገራቸውም ተዘግቧል።

በተጨማሪም ጄኔራል ፃድቃን ወደ 8 ሺሕ የሚጠጉ የመከላከያ ሠራዊት ወታደሮች በህወሓት ኃይሎች መማረካቸውን ቢናገሩም፣ የአገር መከላከያ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ይህ ቁጥር የተጋነነ ነው ብለወታል፡፡ አክለውም ከሠራዊቱ አባላት መካከል በሕዝብ ላይ አንተኩስም ብለው እጃቸውን የሰጡ መኖራቸውንም አብራርተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ሰኞ ሰኔ 28 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው አስፈላጊ ከሆነ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወጣት ኢትዮጵያውያን በትግራይ እንደሚሰማሩ ጠቅሰው፣ ነገር ግን ሰላማዊ መፍትሔ እንደሚሹ ጠቁመዋል። ‹‹በግጭቱ መግፋት እንችላለን። ውጤቱ ግን መግደል ነው። በሁለቱን ወገን ዶላር ይባክናል። በዚህ መንገድ ማሸነፍ አይቻልም›› በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img