አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ሰኔ 29፣ 2013 ― የአዲስ አበባ ፖሊስ እና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን መለያ የለበሱ የፀጥታ ኃይሎች በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ላይ የጅምላ እስር እና እንግልት እየፈጸሙ እንደሚገኙ ተነግሯል፡፡
በጉዳዩ ላይ ዘገባ ይዞ የወጣው አዲስ ስታንዳርድ፣ ይኸው ተግባር በከተማው ሰሚት በሚገኝና የትግራይ ተወላጆች በሚበዙበት አካባቢ ላይ መፈጸሙን ከዓይን እማኞች መስማቱን አመልክቷል፡፡ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦችም በፖሊስ እንግልት እንደተፈጸመባቸው ነው ዘገባው ያመለከተው፡፡
የጅምላ እስሩ በተለያዩ የአዲስ አበባ ከተማ አካባቢዎች በሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ላይ እየተፈፀመ እንደሚገኝ መረጃዎች የሚያመለክቱ ሲሆን፣ ብዙዎቹ ታሳሪዎችም ወደ አዋሽ አርባ ካምፕ ሳይወሰዱ እንዳልቀሩ ምንጮች ለአምባ ዲጂታል ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ሰኔ 26 ባወጣው መግለጫ ‹‹በአዲስ አበባ ከተማ የትግራይ ክልል ተወላጅ የሆኑ ነዋሪዎችና የሚዲያ ሰዎችን ጨምሮ፣ ሌሎች ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል ተጠርጥረው የታሰሩ ሰዎችን ሁኔታ በመከታተል ላይ›› እገኛለሁ ብሎ ማለቱ ይታወሳል፡፡
ኮሚሽኑ በዚሁ መግለጫው ይህ ‹‹በነዋሪዎች ላይ ማንነትን በመለየት ለጥርጣሬ እና መድልዎ የሚያጋልጥ ተግባር እንዳይሆን ስጋት የሚያሳድር›› መሆኑንም ጠቁሞ ነበር፡፡ አዲስ ስታንዳርድ የኮሚሽኑ የሚዲያ አማካሪ አሮን ማሾ አሁንም ጉዳዩን እየተከታተሉ እንደሚገኙ አረጋግጠውልኛል ብሏል፡፡
ከነዋሪዎች በተጨማሪ ባለፈው ሳምንት በቁጥጥር ስር መዋሉ የተነገረውና በአዲስ ስታንዳርድ ዘገባ የተጠቀሰው የአውሎ ሚዲያ የካሜራ ባለሞያ ሙሴ ሐደራ የትዳር አጋር፣ አሁንም ድረስ ባለቤቷ የት እንደደረሰ አለማወቋን መናገሯ ተመላክቷል፡፡
የካሜራ ባለሞያው የትዳር አጋር ፖሊስ ጋር በማቅናት ባለቤቷ የት እንደደረሰ ጠይቃ ተለቋል የሚል ምላሽ ብታገኝም፣ ነገር ግን እንዳላገኘችውና የተከሰሰው በምን እንደሆነ ለማወቅም ያለበትን ለይቶ ራሱን ማግኘት እንደሚያስፈልግ ተናግራለች፡፡
ድረ ገጹ በጉዳዩ ላይ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እና የፌዴራል ፖሊስ ቃል አቀባዮችን ማግኘቱን ያመለከተ ሲሆን፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ቃል አቀባይ የሆኑት ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ ስለ ጉዳዩ እንደማያውቁ ሲናገሩ፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ቃል አቀባይ በበኩላቸው የፌዴራል ፖሊስ ዜጎች በወንጀል ተሳትፈው ካላገኘ በስተቀር በማንነት ለይቶ በቁጥጥር ስር እንደማያውል ገልጸዋል፡፡
ፎቶ፡ በገላን ኮንዶሚንየም አካባ የሚገኝ ማጎሪያ
የፎቶ ምንጭ፡ አዲስ ስታንዳርድ