Sunday, September 22, 2024
spot_img

የተኩስ አቁም ወሳኔው ከመንግሥት በኩል ቀድሞ የታቀደበት መሆኑን ጠ/ሚ ዐቢይ ተናገሩ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ሰኔ 28፣ 2013 ― ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዛሬው እለት የትግራይ ክልል ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለቀረበላቸው ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል፡፡

ከነዚህ መካከል በክልሉ በመንሥታቸው በኩል የተወሰደው የተናጠል የተኩስ አቁም ወሳኔው ቀድሞ የታቀደበት ነው መሆኑንና ወታደሩም በአንድ ጊዜ ሳይሆን በተለያየ ጊዜ መውጣቱን ተናግረዋል፡፡

ይህንኑ የሰራዊት ማውጣቱን በተመለከተ ከወታደራዊ ዲሲፕሊን እና ምሥጢር አንጻር ነው አስቀድሞ ያልተነገረው ብለዋል፡፡

ወታደር ማውጣት የጀመርነው ከመቀሌ የወጣን ጊዜ አልነበረም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ከአንድ ወር በላይ የፈጀ ሂደት መሆኑን እንዲሁም በአራት ግንባር ተከፍሎ መውጣቱንና ከምርጫ 15 ቀን በፊት ሰፊ ኃይል ቢወጣም ከተምቤን አካባቢ ኃይል ሲወጡ ግን ትኩረት መሳቡን አስረድተዋል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ውስጥ 10 ዓመት፤ 20 ዓመት ጦርነት ማካሄድ ይቻላል፤ ክላሹም፣ ሰውም አለ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የማይቻለው በ5 ዓመት፣ በ10 ዓመት እድገት ማምጣት ነው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

በሌላ በኩል ሕወሃትን በሚመለከት ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ቡድኑ አራት ግልጽ ወሳኝ አደጋዎችን ደቅኖ ነበር በማለት አደጋ ነበሩ ያሏቸውን አብራርተዋል፡፡

የመጀመሪያው አደጋ ሕወሃት በሥልጣን ላይ ከነበረበት በተለየ ከመከላከያ የሚተካከል ተቋም ለመገንባት ወታደር ለማዘጋጀት ሰፊ ስራ መስራቱን፣ ሁለተኛው አደጋ ቅጥረኞችን በየቦታው ማሰማራቱን፣ ሶስተኛው ህዝቡን ለጦርነት የመቀስቀስ ሰፊ ስራ መስራቱን እና በአራተኛነት በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ማድረሱ መሆኑን ዘርዝረዋል፡፡

መከላከያ ሰራዊት ለዋለው ውለታ ቢያንስ ጡት እስከ መቁረጥ መሄድ አልነበረባቸውም ያሉት ዐቢይ፣ ከጦርነቱም በኋላ ቡድኑ ባደረሰው ውድመት ቴሌኮሙኒኬሽን ለማስጀመር 30 ሰው ገደማ መሰዋቱን እንዲሁም መብራት ለመቀጠል ብዙዎች መገደላቸውን አመልክተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዛሬው ፓርላማ በደከምነው ልክ 40 ዓመት የተረጨውን የዘረኝነት መርዝ ልናጸዳው አልቻልንም ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የውጭ ጉዳዮችን በተመለከተ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ሁኔታ በርካታ ቁጥር ያላቸው ኤምባሲዎች እንዲኖራት አይፈቅድም ብለዋል። ስለሆነም አሁን ካሉት ኤምባሲዎች ቢያንስ 30 ያህሉ መቀነስ ይገባቸዋል ያሉ ሲሆን፣ አምባሳደሮቹ በአገራቸው ተቀምጠው ስራቸውን እንዲሰሩ ማድረግ ይገባል ሲሉ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥቆማ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚነስትሩ በተጨማሪም ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን በተመለከተ እና ወቅታዊውን የዓለም ዲፕሎማሲንም አንስተው ማብራሪያ የሰጠ ሲሆን፣ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን ‹‹ልናምናቸው አንችልም›› ብለዋል፡፡

ዲፕሎማሲን በተመለከተም ወቅታዊውን የዓለም ዲፕሎማሲ ሊመረመር እና ሊፈተሽ ይገባል ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ኢትዮጵያ ላይ ያለው ውርጅብኝ ‹‹ለቅሶው ከፍየሏ በላይ ነው›› ከሚባለው በላይ ነው ያሉ ሲሆን፣ በዩክሬን ያለው እና በኢትዮጵያ ካለው ነገር ጋርእንደሚመሳሰል በመጥቀስ፣ ነገር ግን ዩክሬን ላይ ላለው ጉዳይ የሚሰጠው ግብረ መልስ የሚደረገውና ኢትዮጵያ ላይ ላለው የሚደረገው አራምባ እና ቆቦ ነው ብለውታል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img