Saturday, September 21, 2024
spot_img

ኢዜማ መንግሥት ለአገራዊ ውይይት በሩን ክፍት እንዲያደርግ ጠየቀ

አምባ ዲጂታል፣ እሑድ ሰኔ 27፣ 2013 ― የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ሁሉንም ባለ ድርሻ አካላትን ያካተተ ፖለቲካዊ መፍትሄ በሚያስፈልጋቸው አጀንዳዎች ላይ ለሀገራዊ ውይይት በሩን ክፍት እነንዲያደርግ ጠይቋል፡፡

ፓርቲው ባወጣው መግለጫ ‹‹ለዚህም እንዲረዳ ከሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ጋር የሚታዩትን ልዩነቶች በማጥበብ በመቀራረብና በመመካር ሀገር የመምራት ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ›› በጥብቅ አሳስቧል፡፡

ፓርቲው ‹‹ሀገርን እና ሕዝብን ለመታደግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ ሊሰሩ የሚገባበት ወሳኝ ወቅት ላይ ደርሰናል›› ባለበት መግለጫው፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት በኢሕአዴግ ውስጥ ያለፉ ሒደቶችን አስታውሷል፡፡

በዚህ ሒደት የሕወሃት አመራሮች የለውጡ ሂደት ከመጀመሩ በፊት የነበራቸውን ድርጅታዊ የበላይነት እየሸረሸረ በመምጣቱ ወደ ትግራይ ክልል በማፈግፈግ አቅማቸውን ማጎልበትና የለውጡ አመራርን በመፈታተን በለውጡ አካሄድ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ሲዘጋጁ ነበር ያለው ፓርቲው፣ በዚሁ ሰበብ በተፈጠረው ውጥረት የሀገርን ህልውና እና ቀጣይነት የተፈታተኑ ችግሮች ማጋጠሙንና ከነዚህ ችግሮች መካከል በዋነኛነት ባለፈው ጥቅምት ወር በሀገራችን ሰሜናዊ ክፍል በትግራይ ውስጥ የተከሰተው ግጭት ጠቅሷል፡፡

ይህንነኑ ተከትሎ ሕወሃት ወደ በረሃ ሲወርድ የተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ላለፉት ስምንት ወራት የክልሉን ሕዝብ ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል ምንም ዓይነት የፖለቲካ ማረጋጋት ሥራ ያልሠራ እና ለችግሩ መባባስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገ መሆኑን መገንዘብ እንደሚቻል ኢዜማ ገልጧል፡፡

በተጨማሪም ጊዜያዊ አስተዳደሩ ሕዝቡን ከማረጋጋት እና ችግሩን ከመቅረፍ ይልቅ ብልጽግና ፓርቲን ለመትከል የተደረገው መፍጨርጨር ችግሩን አወሳስቦታል ያለውኢዜማ፣ የሕግ ማስከበር እርምጃው ከተጀመረ በኋላ በክልሉ ውስጥ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን እና ዜጎች ወደመደበኛ ሕይወታቸው በተቻለው አጭር ጊዜ እንዲመለሱ ለማስቻል ሕወሃት ላይ እርምጃ ከመውሰድ ባሻገር ታስቦበት እና ታቅዶ የተተገበረ የተቀናጀ ግልፅ ተግባር አለመኖሩ፣ ግጭቱን በተበታተነ መልኩ ወደሚደረግ ሽምቅ ውጊያ ስልት የቀየረው ሕወሃት ውጊያ መቀጠሉ፣ በክልሉ ውስጥ ያለው ሰብዓዊ ቀውስ እየጨመረ ከመሄዱ ጋር ተደማምሮ በክልሉ ሰላምን ማረጋገጥ እና ዜጎችን ወደመደበኛ እንቅስቃሴ መመለስ ሳይቻል መቆየቱንም አንስቷል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ችግሩ ተባብሶ በቀጠለበት ሁኔታ ውስጥ የፌደራል መንግስት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የተናጠል የተኩስ ማቆም ጥያቄን በመቀበል መከላከያ ሠራዊቱን በቅጽበት አብዛኛው የክልሉ ክፍል ማስስጣቱን ያስታወሰው መግለጫው፣ ይህ ሲሆን በክልሉ ውስጥ የሚኖሩ ሰላማዊ ዜጎችን (ተማሪዎችን፤ የጊዜያዊ መንግሥት የታችኛው መዋቅር ሰራተኞችን…ወዘተ) እና የአገሪቱ ሰላምና ሉዓላዊነት ላይ ሊያመጣ የሚችለውን ችግር በቅጡ ከግምት ባላስገባ እና በተቻኮለ መልኩ መሆኑ በትግራይ ክልል የደረሰው ቀውስ ከክልሉም በላይ እንድምታ ወዳለው ከፍተኛ ምዕራፍ ሊሸጋገር ችሏል ነው ያለው፡፡

ከዚህ አንጻር የኢዜማ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በወቅታዊ የትግራይ ክልል ሁኔታና ይበልጡንም ደግሞ ይህ የተፈጠረው አዲስ ሁኔታ ባጠቃላይ በሀገሪቱ ሰላም፤ የፖለቲካ መረጋጋት፤ ሀገራዊ አንድነት እንዲሁም በቀጠናው የወደፊት ሰላም ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ሀገራዊ ፈተናዎችንና የሚያስከትላቸውን እንድምታዎች ገምግሜያለው ያለው ኢዜማ፣ ሊሆኑ ይችላሉ ያላቸውን ነገሮች አስቀምጧል፡፡

ፓርቲው ካስቀመጣቸው የቢሆን ግምቶች መካከል ከሀገሪቱ ዘላቂ ጥቅም አንጻር ጥሩ ሊባል የሚችል የቢሆንስ ግምት፣ መንግሥት እንደሚለው ይህ የተናጠል የተኩስ ማቆም በክልሉ ያለውን የሰብአዊ ቀውስ ለመታደግና የእርሻ ጊዜው እንዳያልፍና ወደ ከፋ የችጋር ሁኔታ ውስጥ እንዳይገባ በማሰብ የተደረገ እርምጃ መሆኑን በትግራይ ያሉት ታጣቂዎችም ሆነ ማኅበረሰቡ ተረድቶና አምኖበት በክልሉ ምንም ዓይነት የኃይል እንቅስቃሴ ቆሞና ሁሉም አካላት (የፌደራል መንግሥት፤ እርዳታ ሰጪ ተቋማት፤ የትግራይን አስተዳደር የተረከበው አካል…ወዘተ) ትኩረታቸውን ወደዚያ አድርገው በተቻለ መጠን በአጭር ጊዜ ችግሩን መቅረፍ የሚችሉበት፤ ከዚያም በኋላ ቀጣይ የፖለቲካ ጉዳዮችን በውይይት ለመፍታት ፍላጎት የሚታይበትና ወደ ሰላማዊ መፍትሄ የሚኬድበት መሆኑን ጠቁሟል፡፡

ምንም እንኳን ይህ ቢሆንስ ባጠቃላይ ሰላምን ከማንገሥና የሰብዓዊ ቀውሱን ለመታደግ ጥሩ የሚባል ቢሆንስ ቢሆንም እስከዛሬ በተለይም ባለፉት ሦስት ዓመታት ካየናቸው የባለድርሻ አካላት ባሕርይ አንጻር ሲታይ (ከመንግሥት፤ ከሕወሃት፤ ከእርዳታ ሰጪ አካላት…ወዘተ) በተለይም ደግሞ ሕወሃት በነኝህ ሦስት ዓመታትም ሆነ ከዚያ በፊት ለ27 ዓመታት በማዕከላዊ መንግሥት ሥልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ ጭምር ሲጫወት የነበረውን አፍራሽ ሚና በቅርብ ለተመለከተ፤ እውን የመሆን ዕድሉ እጅግ የመነመነ ነው ብሎታል፡፡

በሁለተኝነት ፓርቲው ያስቀመጠው ግምት፣ በትግራይ ያለው ያልጠራ ሁኔታ እንደቀጠለና የትግራይ አማጺዎች ከትግራይ ውጭ ሊያደርጉ የሚሞክሩት ግጭቱን የማስፋት ሙከራ (ወደ አጎራባች ክልሎች ወይም ከዚያም ዘልቆ ለመግባት) በፌደራል መንግሥቱ እየተመከተና እየከሸፈ የሚቀጥልበት፤ ግልጽ አሸናፊ የማይኖርበት ሁኔታ ነው ያለ ሲሆን፣ ይህ ግምትከመጀመሪያው የተሻለ የመሆን ዕድል ያለው የቢሆንስ ግምት ሕወሃት በአማራና በአፋር ክልሎች እና በኤርትራ በኩል መጠነኛ ትንኮሳዎችን የሚፈጽምበት፣ በትግራይ ውስጥም ከፍተኛ ቀውስ የሚፈጥርበት ሁኔታ ከተፈጠረ የፌደራል መንግሥት መከላከያ ሠራዊት ተመልሶ ለመግባት ሊገደድ ስለሚችል ይህ ሁኔታ ከሕውሃት ባሕሪ እና ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር የመሆን እድሉ የማይናቅ መሆኑን ጠቅሷል፡፡

በዚህ ሁኔታ በአንዳንድ ከተማዎች ሕግና ሥርዓት የማስከበሩ ደረጃ ዝቅተኝነት የሚፈጥረውን አጋጣሚ በመጠቀም ዘረፋዎች ሊካሄዱ እንደሚችል፣ እለት እርዳታ የሚያስፈልጋቸው የክልሉ ነዋሪዎች በሚፈለገው ደረጃ እርዳታ ሳያገኙ ቀርተው ለከፍተኛ አደጋ ሊጋለጡ እንደሚችሉ፣ መሰረታዊ ለኑሮ የሚያስፈልጉ አገልግሎቶች፣ የውሃ፣ የመብራት፣ ህክምና፣ ግብዓቶች ማግኘት የማይቻልበት ሁኔታ ሊፈጠር የሚችልበት ዕድል ከፍተኛ በመሆኑ፣ የክልሉ ሕዝብ ለችግር የሚጋለጥበት ሁኔታ ሊኖር የሚችል መሆኑን፣ የክልሉን አስተዳደር እንደገና ለማቋቋም ጊዜ የሚወስድና አስቸጋሪ ሊሆን ስለሚችል የክልሉ ሕዝብ ለረጅም ጊዜ ምንም ዓይነት አስተዳደራዊ አገልግሎት ሊያገኝ የማይችልበት ሁኔታ ሊፈጠር የሚችል በመሆኑም፣ እንዲሁም መንግሥት የወሰደውን ክልሉን ለቆ የመውጣት እርምጃ የሚቃወሙና ተመልሶ እንዲገባ ጫና የሚያደርጉ ሀገራት ሊኖሩ ስለሚችሉ፣ የመሆን እድሉ የተሻለ ይሁን እንጂ በክልሉና ባጠቃላይ በሀገሪቱ ከብሄር ፖለቲካ ጋር ተያይዞ የመጣውን አደጋ በዘላቂነት የማይፈታ፤ ሀገሪቱን ቀስ እያለ ውስጧን እንደሚበላ በሽታ ከመግደሉ በፊት መፍትሄ የሚፈልግ ስለሆነ ለሀገሪቱ የተሻለ መፍትሄ በፍጹም ሊሆን አይችልም ብሏል፡፡

ሦስተኛውና ኢዜማ እጅግ የከፋው ነው ያለው የቢሆንስ ግምት ሕወሃት ክልሉን፣ አገሪቱንና ቀጠናውን ለማተራመስ ከሌሎች አክራሪ ሃይሎች ጋር ጥምረት የሚፈጥርበት ሁኔታና አልፎም ለሀገሪቱ የውጭ ጠላቶች መሳሪያ በመሆን በሀገሪቱም ሆነ ባካባቢው ፍጹም አደገኛ የሆነ ሁኔታ ሊፈጠር የሚችልበት ሁኔታ መሆኑን አመልክቷል፡፡

ይህ ሁኔታ ከሕወሃት የፀብ አጫሪነት ባሕሪ የተነሳ፣ አሁን ክልሉ፣ አገሪቱና ቀጠናው ካሉበት ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ሲታይ እና ከዚህም በተጨማሪ የውጭ አገራት፣ የአገራት ማኅበራት ሁኔታውን ባላገናዘበ መልኩ እያደረጉ ያሉት ጣልቃ ገብነት ሲታከልበት የመፈጠር ዕድሉ አነስተኛ እንኳን ቢሆን፤ «የተሻለውን ተስፋ አድርግ ግን ለመጥፎው ተዘጋጅ» እንደሚባለው አባባል የኢትዮጵያ መንግሥት፤ የኢትዮጵያ ሕዝብም ሆነ በፖለቲካ ጉዳይ ከመንግሥት ጋር ልዩነት ያላቸው ግን የሀገሪቱን ሰላምና አንድነት የሚፈልጉ ኃይሎች ሁሉ በመተባበርና ያለ የሌለ አቅማቸውን በማሰባሰብ ችግሩ ከመፈጠሩ በፊት ሊቀጩት የሚገባ ነው ብሎታል፡፡

ኢዜማ በዚህ እጅግ ፈታኝ በሆነ ወቅት ላይ በሀገሪቱ ላይ የተደቀነውን አደጋ ለማለፍ ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት የሚያስፈልጋቸውን ትዕግስት፣ ጥበብ፣ አርቆ አሳቢነትና ቁርጠኝነት ከግምት ማስገባት ያስፈልጋል ያለ ሲሆን፣ በመንግሥት በኩል ሀገርን በመምራት ሂደት ውስጥ በየቦታው የሚዝረከረኩ አሠራሮችን መስመር በማስያዝ ጥበብ በተሞላበት መልኩ ሀገርን ማስተዳደር እንደሚጠበቅና ከዚህ አንጻር ሁሉንም ባለ ድርሻ አካላትን ያካተተ ፖለቲካዊ መፍትሄ በሚያስፈልጋቸው አጀንዳዎች ላይ ለሀገራዊ ውይይት በሩን ክፍት ማድረግ ይኖርበታል ብሏል፡፡ ለዚህም እንዲረዳ ከሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ጋር የሚታዩትን ልዩነቶች በማጥበብ በመቀራረብና በመመካር ሀገር የመምራት ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ በጥብቅ አሳስቧል፡፡

በሌላ በኩል መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በያለበት መሠረቱን ዜግነት ባደረገ መልኩ ተደራጅቶ ራሱን፣ ቤተሰቡን፣ አካባቢውንና ሀገርን ከተለያዩ ጥቃቶች መጠበቅ ግድ እንደሚለው ፓርቲው አሳስቧል፡፡

በተጨማሪም ሀገርን ከመበታተን ለመታደግ ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የሚያደርገውን ብሔራዊ ጥሪ ተቀብሎ በመከላከያ፣ በፖሊስ እና በሌሎች የፀጥታ ተቋማት በመሳተፍ የዜግነት ድርሻውን ሊወጣ ይገባዋል ብሏል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img