Sunday, October 6, 2024
spot_img

ኦፌኮ እና ኦነግ የኦሮሚያ ክልላዊ ሽግግር መንግሥት መመስረታቸውን አስታወቁ

– የመንግሥት ተወካዩ የፓርቲዎቹን የሽግግር መንግሥት ምሥረታ ‹‹ቀልድ›› ነው ብለውታል

አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ሰኔ 26፣ 2013 ― ከቀናት በፊት ከተካሄደው አገራዊ ምርጫ ቀድመው ራሳቸውን አግልለው የነበሩት የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) እና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) በኦሮሚያ ክልል ለ3 ዓመት የሚቆይ የኦሮሚያ ክልላዊ ሽግግር መንግሥት መመስረታቸውን አስታውቀዋል፡፡

ራሱን ‹‹የሽግግር ምክር ቤት›› ብሎ የሰየመው ቡድን ባወጣው መግለጫ፣ የሽግግር መንግሥቱ ምክር ቤት ከሁለቱ ፓርቲዎች፣ ከሲቪል ማኅበራት፣ ከገዳ እና ሃይማኖት ተቋማት ከሀገር ሽማግሌዎችና ከሌሎች ኅብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ 337 ተወካዮች እንዳሉት ነው የገለጸው፡፡

መግለጫው የሽግግር መንግሥቱን አወቃቀርና ፕሮግራም የዘረዘረ ሲሆን፣ ‹‹የሽግግር መንግሥቱ›› የኦሮሚያን ሕገ መንግሥት እንደሚያከብር ተገልጧል፡፡

ሁለቱ ፓርቲዎች ሽግግር መንግሥቱን ያቋቋሙት፣ ‹‹መንግሥት ኦሮሚያን የጦርነት ቀጠና በማድረጉ፣ ሕጋዊ ክልላዊ መንግሥት አለ ብለው ስለማያምኑና አገሪቱ ያለችበት ውጥንቅጥ ግምት ውስጥ በማስገባት›› እንደሆነ መግለጫው ያትታል፡፡

ይህንኑ የፓርቲዎቹን መግለጫ ተከትሎ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ አጭር ምላሽ ያሰፈሩት የገዢው ብልጽና ፓርቲ የኦሮሚያ ጽሕፈት ቤት ቃል አቀባዩ አቶ ታዬ ደንደኣ፣ ‹‹ሽግግር የሚባል ቀልድ የለም›› ብለዋል፡፡

‹‹በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ከሞላ ጎደል ነፃ ምርጫ ተደርጓል›› ያሉት ታዬ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ህዝብ ከለሊት እስከ ለሊት ተሰልፎ የሚፈልገዉን መርጧል፤ ባዳዎችን ተማምኖ ከምርጫዉ ራሱን ያገለለ ባንዳ ደግሞ በምርጫ ማግስት ‹የሽግግር መንግስት› እያለ ይቀልዳል›› ሲሉ አስፍረዋል፡፡

አክለውም ‹‹አሁን ላይ ነገሮችን ግልፅ ማድረግ ያስፈልጋል፤ በኢትዮጵያ ህዝብ ሉዓላዊ ስልጣን አይቀለድም፤ የነፃነትን ድንበር በመጣስ ሀገርን አተራምሶ የዜጎችን ሕይወትና ንብረት በማጥፋት ተጠርጥሮ የታሰረ እጩ ወንጀለኛም ከሕግ ውጭ በግርግር አይፈታም፤ ‹ሽግግር› የሚባል የባዳና የባንዳ ቀልድ አይሰራም›› ማለታቸውም ተመላክቷል፡፡

አሁን በኦሮሚያ ክልል የሽግግር መስርተናል ያሉት የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ እና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ከምርጫው ለማግለላቸው እንደ ምክንያት ካቀረቡት መካከል በርካታ አመራሮች እና እጩዎቻቸው በመታሠራቸው መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

ከታሠሩት መካከል የኦፌኮ አመራር አባሎቹ አቶ ጃዋር መሐመድ እና አቶ በቀለ የሚገኙበት ሲሆን፣ ከኦነግ በኩል ቃል አቀባዩ በቴ ኡርጌሳን ጨምሮ ሌሎችም በእስር ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img