አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ሰኔ 25፣ 2013 ― የተወሰኑ የመንግሥት ተቋማት ኃላፊዎች የተለያዩ ሰበቦችን በመፈጠር ኦዲት ላለመደረግ ፈቃደኛ አለመሆናቸው ሊቆም እንደሚገባ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ማሳሰቡ ተሰምቷል፡፡
ይህ ከወትሮ በተለየ ሁኔታ እየታየ ነው የተባለው ችግር በፍጥነት ካልታረመ ጉዳቱ ከፍተኛ በመሆኑ፣ ፓርላማው ከፌዴራልና ከክልል መንግሥታት አመራሮች ጋር በመነጋገር ለችግሩ አፋጣኝ ዕልባት እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማክሰኞ ሰኔ 22፣ 2013 ባካሄደው 16ኛ መደበኛ ስብሰባው፣ የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች የ2012 በጀት ዓመት የፋይናንስና የክዋኔ ኦዲት አፈጻጸምን በተመለከተ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ያቀረበውን ሪፖርት አዳምጧል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ ሁለት ሰዓታትን ያህል በፈጀው የ61 ገጽ የተቋማት ኦዲት ግኝት ሪፖርት፣ በበርካታ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ከሕግና ከአሠራር ውጪ የተከናወኑ ተቋማዊ ግድፈቶች መገኘታቸውን አመልክተዋል፡፡
ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ከጠቀሷቸው ግድፈቶችና በወቅቱ ያልተወራረዱ ወይም ከማን እንደሚሰበሰቡ ካልታወቁ ውዝፍ ተሰብሳቢ ሒሳብ ከተገኘባቸው የመንግሥት ተቋማት መካከል፣ የብሔራዊ አደጋ ሥጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን 1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር፣ ጤና ሚኒስቴር 1ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር፣ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር 614 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር 402 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር፣ እንዲሁም ጎንደር ዩኒቨርሲቲ 385 ሚሊዮን ብር ተገኝቶባቸዋል፡፡
በተጨማሪም የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ 336 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር፣ የአገር አቀፍ የትምህርትና ምዘና ፈተናዎች ኤጀንሲ 296 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር፣ የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር 174 ሚሊዮን ብር፣ የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት 126 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ከማን እንደሚሰበስብ በውል በማይታወቅ ሁኔታ በውዝፍ ተሰብሳቢ መባሉን ለፓርላማው የቀረበው ሪፖርት ያሳያል፡፡
በሌላ በኩል በገቢዎች ሚኒስቴርና በጉምሩክ ኮሚሽን ዋና መሥሪያ ቤቶችና በሥራቸው ባሉ 12 ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች፣ እንዲሁም በሌሎች 31 መሥሪያ ቤቶችና በአንድ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት መሰብሰብ የነበረበት ነገር ግን ያልተሰበሰበ 390 ሚሊዮን ብር መገኘቱም በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡
በተመሳሳይ በገቢዎች ሚኒስቴር ገቢ ሰብሳቢ መሥሪያ ቤቶችና ድርጅቶች በወጣው ሕግና ደንብ መሠረት፣ የመንግሥትን ገቢ በአግባቡ መሰብሰባቸውን ለማረጋገጥ በተደረገ ኦዲት፣ በሚኒስቴሩ ባሉ ስድስት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶችና በጉምሩክ ኮሚሽን ሥር ባሉ ሌሎች ስድስት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች በታክስ ኦዲት ወይም በድኅረ ዕቃ አወጣጥ ኦዲት ውሳኔ መሠረት ያልተሰበሰበ 7 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር መገኘቱ ተመልክቷል፡፡
መንግሥት ከውጭ አገር በብድር ያገኘውን ገንዘብ በመልሶ ማበደር ስምምነት መሠረት ለልማት ድርጅቶች ያበደረውን ገንዘብ በገቡበት ውል መሠረት ወቅቱን ጠብቀው ተመላሽ ባለማድረጋቸው፣ ከተለያዩ ሰባት ድርጅቶች ከ2001 እስከ 2012 ድረስ 14 ቢሊዮን ብር በወቅቱ አለመሰብሰቡን ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ አስረድተዋል መባሉን የዘገበው ሪፖርተር ጋዜጣ ነው፡፡