Sunday, September 22, 2024
spot_img

በትግራይ የሚገኙ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ደኅንነት አሳስቦናል ያሉ ወላጆች እና ተማሪዎች ሰልፍ አደረጉ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ሰኔ 24፣ 2013 ― በዛሬው ዕለት ቁጥራቸው ከ200 በላይ የሚገመት ወላጆች አዲስ አበባ በሚገኘው የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ደጃፍ ላይ በመገኘት ‹‹ልጆቻችን አሁን ስላሉበት ሁኔታ የምናውቅበት መንገድ ይመቻች›› በሚል ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡

ዓላማቸው ‹‹ልጆቻችን አሁን ስላሉበት ሁኔታ የምናውቅበት መንገድ ይመቻች›› የሚል ሐሳባቸውን ለሚመለከተው አካል ማሰማት መሆኑን የተናገሩት ተሰብሳቢዎቹ፣ የፌደራል መከላከያ ሰራዊት መቀሌን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ በትግራይ ክልል የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩ ልጆቻቸውን ሁኔታ ማወቅ አለመቻላቸው ከፍተኛ ስጋት እንደፈጠረባቸው መናገራቸውን አዲስ ዘይቤ ድረ ገጽ ከወላጆቹ መስማቱን ዘግቧል፡፡

በሌላ በኩል ‹‹ጓደኞቻችን መንገድ ላይ ታግተዋል›› ያሉ የራያ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ሁኔታውን በማስመልከት ዛሬ በወልዲያ ከተማ ሰልፍ ማድረጋቸው ተሰምቷል፡፡ እነዚህ ተማሪዎች በሰልፉ ሳይወጡ ስለቀሩና ታግተዋል ስላሏቸው ተማሪዎች ደህንነት ጉዳይ ጠይቀዋል፡፡ በቁጥር 220 ገደማ ነን የሚሉት ተማሪዎቹ ባደረባቸው ስጋት ምክንያት ዩኒቨርስቲያቸውን ባሳለፍነው ሰኞ ሰኔ 21፣ 2013 እኩለ ሌሊት ላይ ለቀው በእግር ጉዞ መሆኒ ከዚያም በአላማጣ አድርገው ወልዲያ በተሸከርካሪ መግባታቸውን አል ዐይን ከተማሪዎቹ ሰምቻለሁ ብሎ ዘግቧል፡፡

ሚዲያው ዩኒቨርሰቲውን ለቀው ከወጡት መካከል የሆነችና አናገርኳት ያላት የ3ኛ ዓመት የስነ ዜጋ እና ሥነ ምግባር ተመራቂ የሆነችው ስንዱ እንዳለችው፣ ለቀው ከወጡት ተማሪዎች መካከል አብዛኞቹ ተመራቂ ተማሪዎች ናቸው፡፡

ዩኒቨርሲቲውን ለቀው ሲወጡ እስከ መሆኒ በእግራቸው፣ ከዚያም ከተማው ሳይገቡ በአቋራጭ መንገድ ሲጓዙ የሚሳፈሩበት ተሽከርካሪ አግኝተው ወደ አላማጣ ማቅናታቸውን ገልጻለች፡፡

በጉዟቸው ለመሆኒ እስከተቃረቡበት ጊዜ ድረስ፣ አብረዋቸው ሲጓዙ የነበሩና ውሃ ለመጠጣት በሚል ወደ ኋላ የቀሩ 7 ተማሪዎች መንገድ ላይ ታግተው ተለይተው መቅረታቸውንም ተናግራለች፡፡

ይህንኑ ታግተው ከነበረበት አምልጠው ከመጡና ንብረታቸው መወሰዱን ከተናገሩ ሦስት ተማሪዎች ማረጋገጧን የተናገረችው ተማሪዋ፣ ቀሪዎቹ 4 ታጋች ተማሪዎች ያሉበትን ሁኔታ ማወቅ አለመቻሏንም ገልጻለች፡፡

ተማሪዎቹ ሁኔታውን በማስመልከት ዛሬ በወልዲያ ከተማ ሰልፍ ያደረጉ ሲሆን፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወ/ሮ አመለወርቅ ሕዝቄል በራያ ዩኒቨርስቲ ብቻ ሳይሆን፣ በትግራይ ክልል በሚገኙ በሌሎቹም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጉዳይ ላይ ምክክር እየተደረገ እንደሆነ መግለጻቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img