Sunday, October 13, 2024
spot_img

የአሜሪካ ሴኔት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ የአፍሪካ ጉዳዮች ዋና አስተባባሪ በወቅታዊ የአገሪቱ ጉዳይ የአብን አመራሮችን አነጋገሩ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ሰኔ 24፣ 2013 ― የአሜሪካ ሴኔት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ የአፍሪካ ጉዳዮች ዋና አስተባባሪው ጆን ቶማስስውስኪ፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ሊቀመንበሩ አቶ በለጠ ሞላ እና ምክትላቸው አቶ ዩሱፍ ኢብራሂምን በወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳዮች ዙሪያ ማነጋገራቸውን ፓርቲው አስታውቋል፡፡

በሸራተን አዲስ በተደረገውና ‹‹አንኳር በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያተኮረና ፍሬያማ›› ነበር በተባለው ውይይት፣ ‹‹በተለይ የአማራ ልዩ ኃይልን ተጋድሎና መስዋእትነት እንዲሁም የአማራ ብሔርተኝነት፣ የአብን ትግልና ፍላጎት ላይ ግልጽ ያልነበሩ በርካታ ቁምነገሮች›› መነሳታቸውን ፓርቲው አመራሮቹን ጠቅሶ ገልጧል፡፡

አክሎም በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን ‹‹የማህበረ ፖለቲካ ሁኔታ በማንሳት በቀጣይ መሰራት ባለባቸው መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ውይይት የተደረገበትና ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተለይም በአሜሪካ መንግስት በኩል መወሰድ ያለባቸውን አቋሞች በተመለከተ ወሳኝ ምልከታዎች ቀርበው ውይይትና መተማመን ላይ የተደረሰበት›› ነበር ብሏል፡፡

በሌላ በኩል ፓርቲው ከቀናት በፊት በተደረገው ሀገራዊ ምርጫ ላይ የቀረቡ ቅሬታዎችን ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አቅርቦ፣ ከቦርዱ ከፍተኛ አመራሮችና ባለሙያዎች ጋር ውይይቶችን ማድረጉንም አስታውቋል፡፡

በዚህ ውይይት ከቦርዱ ሰዎች ጋር ‹‹በአቤቱታ አቀራረብና በማስረጃ ጉዳዮች ዙሪያ በርካታ ሐሳቦችን ለመለዋወጥ ችለናል›› ያለው ፓርቲው፣ ‹‹ለሀገር ሰላምና ደህንነት ግንባር ቀደም ትኩረት›› ስለምሠራ፣ በምርጫው ወቅት ያጋጠሙ ችግሮችን ‹‹ሕጋዊ መስመሮችን ተከትሎ እልባት ለመሻት›› ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ጠንካራ ስራ እያከናወንኩ እገኛለሁ ብሏል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img