አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ሰኔ 23፣ 2013 ― የአገር መከላከያ ሰራዊት ከሰሞኑ የታወጀው የተናጠል ተኩስ አቁም ስምምነት እና ወታደሮችን ከመቀሌ የማስወጣቱ ሂደት በተመለከተ በሰጠው መግለጫ፣ ሕወሓት በወልቃይት እና ራያ በኩል እዋጋለሁ ካለ የከፋ እርምጃ እንደሚወሰድበት አስታውቋል፡፡
የመከላከያ ሰራዊት ግንባታ ስራዎች ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጀኔራል ባጫ ደበሌ እንደተናገሩት፣ ‹‹ሕወሃት ወደ ወልቃይት እና ራያ እንዳይመጣ ሰራዊቱ በተጠንቀቅ ቆሟል›› ብለዋል፡፡
በዛሬ መግለጫ የሰራዊቱ ከትግራይ ክልል መውጣት ጠቃሚ እንደሆነ የገለጹት ሌተናል ጀኔራል ባጫ ደበሌ፣ ሰራዊቱ አሁን ወጣ እንጂ፣ ለመውጣት ከታሰበ መቆቱን ገልጸዋል፡፡ ሕወሃት አሁን ላይ ስጋት እንዳልሆነም ነው ያመለከቱት፡፡
‹‹ሕወሃት ትንኮሳ ካደረገ ምላሹ የእጥፍ እጥፍ ነው የሚሆነው›› ያሉት ሌተናል ጀኔራል ባጫ፤ ቡድኑ መጀመሪያ ያቀደው፤ በአማራ እና በአፋር ክልል አድርጎ አዲስ አበባ መግባት እንደነበር ገልጸዋል፡፡ አሁን ላይ ይህ ስጋት ሙሉ ለሙሉ ተወግዷል ነው ያሉት፡፡ አሁን ላይ ህወሃት ይጠናከል የሚለው የሚያሳስብ ነገር እንዳልሆነ የገለጹ ሲሆን፣ ሆኖም የኢትዮጵያ ሰራዊት ለሁሉም ነገር ዝግጁ መሆኑ ተናግረዋል፡፡
መንግስት ህወሃት እንዳይጠናከር ብቻ አይደለም እንዳይኖርም እንደሚሰራ ያነሱት ሌተናል ጀነራሉ፣ ትንኮሳ ከመጣ ‹‹የገቡበት እንገባለን፤ ወደውጭ ሚወጡበት ምንም በር የለም›› ብለዋል፡፡
ህወሃት ከዚህ በኋላ መሳሪያ ሊያገኝ የሚችልበት ምንም መንገድ እንደሌለና ሁሉም መንገዶች መዘጋታቸውን ሌተናል ጀኔራል ባጫ ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል ኤርትራ ጦሯን ብታስወጣም ህወሃት ግን ኤርትራን ‹‹ተከትዬ እወጋለሁ እያለ“ መሆኑን በዛሬው መግለጫ ላይ መነሳቱን አል ዓይን ዘግቧል፡፡
ሬውተርስ የሕወሓት ቃል አቃባይ የሆነውን ጌታቸው ረዳን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ ህወሓት የትግራይ ዋና ከተማ መቀሌን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሩንና ሁሉም አካባቢ ጠላት ካለው ኃይል ነጻ እስከሚሆን ድረስ ወደ ደቡብ ወደ ምሥራቅ እንደሚንቀሳቀሱ ተናግረዋል፡፡