Friday, November 22, 2024
spot_img

በአማራ ህዝብ መቃብር ላይ ካልሆነ ዳግም ተከዜን የሚሻገር የሕወሃት ኃይል እንደማይኖር ኮለኔል ደመቀ ዘውዴ ተናገሩ

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ሰኔ 23፣ 2013 ― በአማራ ክልል የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ የሆኑት ኮ/ል ደመቀ ዘውዴ በአማራ ህዝብ መቃብር ላይ ካልሆነ ዳግም “ተከዜን” የሚሻገር የሕወሃት ኃይል እንደማይኖር ተናግረዋል።

የአማራ ህዝብ ለዘመናት ተጭኖበት ከነበረው መከራና ግፍ ለመላቀቅ ተመን የለሽ መስዕዋትነት ከፍሏል ያሉት ኮለኔል ደመቀ፣ ለነጻነቱ ሲልም በከፈልነው ዋጋ ላይ ሒሳብ ለማወራረድ የሚሞክር አካል ካለ ጠቡ ከትህነግ ቡድን ጋር ብቻ ሳይሆን ስምምነት ከፈጸመው አካል ጋር ጭምር መሆኑን ገልጸዋል።

ኮለኔል ደመቀ በኢትዮጵያ ህዝብ ወኪሎች ፊት ቀርቦ አሸባሪ ተብሎ ከተፈረጀ ቡድን ጋር መንግስታዊ የተኩስ አቁም ስምምነት ማድረግ ከአሸባሪዎች አገር የማፍረስ ዓላማ እና ፍላጎት አይተናነስም ያሉ ሲሆን፣ ከአሁን በኋላ በአማራ ህዝብ የህልውና ላይ ሒሳብ ለማወራረድ የሚሞክር መንግሥታዊም ይሁን አሸባሪ ቡድን ካለ ራሱ ይዋረዳል ብለዋል።

አክለውም በተለይም አሸባሪው የሕወሃት ቡድን በሀገር ላይ ከፈጸመው ግፍ በተለየ ሁኔታ በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ አማራ ህዝብ ላይ ለዘመናት ሲፈጽም የኖረው ግፍና በደል በዚህ መለስ የሚባል አይደለም፣ ታሪክ ይቅር የማይለው ሰብአዊና ቁሳዊ በደል እንደፈፀመ አስታውሰዋል።

የኮለኔል ደመቀ ንግግር የመጣው ከትላንት በስትያ መቀሌን ዳግም መያዛቸው የተነገረው የሕወሃት ተዋጊዎች “ጠላት” ያሏቸውን ኃይሎች ለመውጋት እስከ ኤርትራ እና አማራ ክልል ድረስ ሊዘምቱ እንደሚችሉ የሕወሃት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ ለሮይተርስ መናገራቸውን ተከትሎ ነው።

በተመሳሳይ በትላንትናው እለት የብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ጽሕፈት ቤት በራሳቸው መስዋትነት ነፃነታቸውን ያስከበሩ የአማራ አካባቢዎች ናቸው ያላቸውን ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምትና ራያን ከሕግ ውጭ በጉልበት ወስዶ ለመጠቅለል ፍላጎት ካለ ለነፃነቱ ሲል ዋጋ የማይከፍል አማራ እንደሌለ ባወጣው መግለጫ አሳውቋል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img