አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ሰኔ 22፣ 2013 ― የብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ጽሕፈት ቤት በራሳቸው መስዋትነት ነፃነታቸውን ያስከበሩ የአማራ አካባቢዎች ናቸው ያላቸውን ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምትና ራያን ከሕግ ውጭ በጉልበት ወስዶ ለመጠቅለል ፍላጎት ካለ ለነፃነቱ ሲል ዋጋ የማይከፍል አማራ እንደሌለ የአማራ ብልጽግና ባወጣው መግለጫ አሳውቋል።
ፓርቲው የአማራ ህዝብ በሽብርተኞች ሂሳብ እንዲወራረድበት አይፈቅድም የሚል ርእስ በሰጠው መግለጫው፣ የትህነግ አመራሮች በተደጋጋሚ ለደረሰባቸው አሳፋሪ ሽንፈት የአማራን “ኢሊት” ተጠያቂ በማድረግ ሂሳብ እንደሚያወራርዱ ነግረውናል ያለ ሲሆን፣ የሚያወራርዱትን ሂሳብ “ከአማራ ልሂቃን” ጋር ያያይዙት እንጂ እውነታው ግን የአማራን ህዝብ ስለማለታቸው ቅንጣት ታክል ጥርጥር እንደሌለው ገልጿል።
ይሁንና ዛሬ መላው የአማራ ህዝብ በትህነግ ዳግም ሊሰነዘርበት የታሰበውን የጥፋት ሰይፍ በደንብ ተረድቶታል በማለት፣ የብሔራዊ ንቃት ስሜቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ ማደጉን፣ የሞራል ልዕልና ከፍታውን ባለበት ማስጠበቁን በመግለፅ፣ በፍቅር ለመጣ በተለመደ ሰብዓዊ ጀግንነቱ እጁን እንደሚዘረጋና በጥላቻ ለሚመጣ ተገቢውንና የማያዳግም ትምህርት ሰጥቶ ይመልሳል ብሏል።
አክሎም የአማራ ሕዝብ የትኛውንም በቀል ለመበቀል ፍፁም አልተዘጋጀም ያለው የአማራ ብልጽግና፣ ይህ ማለት ግን “ሂሳብ እናወራርዳለን” ባዮችን በዝምታ ይታገሳል ማለት እንዳልሆነና “ከዳተኛና ጸረ-ሕዝብ የሆኑ የትኞቹንም ጠላቶቹን” ያለ ምህረት እንደሚታገል አሳውቋል።
የአማራ ብልጽግና የጠቀሳቸውን አካባቢዎች በጥቅምት ወር መጨረሻ የተነሳውን የፌዴራል መንግሥት እና የሕወሃት ኃይሎችን ጦርነት ተከትሎ የአማራ ልዩ ኃይል መቆጣጠሩ መነገሩ ይታወቃል።
የፓርቲው መግለጫ በትላንትናው እለት መቀሌን ዳግም መያዛቸው የተነገረው የሕወሃት ተዋጊዎች “ጠላት” ያሏቸውን ኃይሎች ለመውጋት እስከ ኤርትራ እና አማራ ክልል ድረስ ሊዘምቱ እንደሚችሉ የሕወሃት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ ለሮይተርስ መናገራቸውን ተከትሎ የመጣ ነው።