አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ሰኔ 22፣ 2013 ― በትግራይ ክልል ውጤታማ የተኩስ አቁም እንደሚተገበር እምነት እንዳላቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ገልጸዋል፡፡
የድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ይህን ያሉት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በስልክ መነጋገረራቸውን በትዊተር ገጻቸው ባሳወቁበት ወቅት ነው፡፡
ጉቴሬዝ ባሳፈሩት መልእክት በክልሉ ለሲቪሎች ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ያስታወቁ ሲሆን፣ ሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች እርዳታው በአፋጣኝ ሊደርስ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በክልሉ ላለው ችግር ከወታደራዊ ይልቅ የፖለቲካ መፍትሔ እንዲመጣ ዋና ጸሐፊው ጥሪቸውን አቅርበዋል።
የአንቶንዮ ጉቴሬዝ መልክእት የመጣው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመሩት የፌዴራሉ መንግስት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ‹‹ወቅቱን የሚመጥን ፖለቲካዊ መፍትሄ መስጠት ያስፈልጋል›› በሚል ላቀረበው የተኩስ አቁም ስምምነት ጥያቄ በአዎንታ መቀበሉን ካስታወቀ በኋላ ነው፡፡
በዚሁ መሠረት የፌዴረል መንግሥት ‹‹አሁን የተጀመረው የእርሻ ወቅት እስኪጠናቀቅ ድረስ የሚቆይ›› ያለ ቅድመ ሁኔታ በሰብአዊነት ላይ የተመሠረተ የተናጠል የተኩስ አቁም ከትላንት ሰኔ 21፣ 2013 ጀምሮ ማወጁን መሳወቁ አይዘነጋም፡፡
ለዚሁ ሲባል ያለፉትን ወራት መቐለ የከረመው የአገር መከላከያ ሠራዊት ከተማዋን ለቆ መውጣቱ መነገሩም ይታወሳል፡፡
ይህንኑ ተከትሎም የሕወሃት ኃይሎች የትግራይ ክልል መቀመጫ የሆነችው መቐለ ከተማን መቆጣጠራቸውን ቃል አቀባዩ አቶ ጌታቸው ረዳ ትላንት ምሽቱን ነግረውናል ብሎ ሬውተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል፡፡