Monday, October 7, 2024
spot_img

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ለፌዴራል መንግስት ጥያቄ ማቅረቡ ተሰማ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ሰኔ 21፣ 2013 ― የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የፌዴራል መንግስት ሰብዓዊነትን መሰረት ባደረገና ተጨማሪ ጉዳት በማያስከትል መልኩ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲያደርግ ጥያቄ ማቅረቡን አስታውቋል።

ኢዜአ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ነግረውኛል እንዳለው፣ ክረምት እየገባ በመሆኑ የትግራይ አርሶ አደር ተረጋግቶ የእርሻ ስራውን እንዲያከናውን፣ የሰብዓዊ ድጋፍ ለተረጂዎች ያለምንም ችግር እንዲደርስ እና ወቅቱን የሚመጥን ፖለቲካዊ መፍትሄ ለመስጠት የፌዴራል መንግስት የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲያደርግ ተጠይቋል።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ ባለፈው ሳምንት በይፋ ጥያቄውን ያቀረበው የክልሉን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ከክልሉ ህዝብ ተወካዮች፣ ከቢሮና የዞኖች አመራር አባላት፣ በተለያየ ቦታ ከሚገኙ የትግራይ ተወላጆች፣ ከትግራይ ምሁራን፣ ከባለሀብቶችና ከሃይማኖት አባቶች ጋር ተከታታይ ምክክር ካደረገ በኋላ ነው ተብሏል።

የህወሃት ቡድን በክልሉም ሆነ በአገሪቷ ላይ የፈጠረው ውስብስብ ችግር ወታደራዊ ብቻ ሳይሆን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መሆኑን ያወሱት አብርሃም በላይ (ዶ/ር)፤ ለዚህም እስከ አሁን በፌዴራል መንግስትና በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የተለያዩ መፍትሄዎች ሲወሰዱ መቆየቱን አብራርተዋል ሲል ዘገባው አክሏል።

እስከአሁን ህግ የማስከበር እርምጃ ከመውሰድ ባሻገር በህግ የሚታዩ ጉዳዮችን በህግ መፍትሄ ለመስጠት ከጥፋት ሃይሉ ወንጀለኛ የሆነውን ለይቶ ወደ ህግ የመቅረብ ስራ ሲከናወን መቆየቱን ተናግረዋል።

በጊዜያዊ አስተዳደሩም ሆነ በፌዴራል መንግስት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎቸን አስታውሰው፤ በቀጣይም ፖለቲካዊ አማራጮችን ታሳቢ ማድረግና የመፍትሄ እርምጃዎችን የመውሰድ አስፈላጊነት ላይ እምነት መኖሩን ጠቁመዋል።

የክልሉ አርሶአደር በዚህ ክረምት ወደ እርሻ ካልገባ የዘር ወቅት ስለሚያልፍ፣ በቀጣይ ገበሬው ለዓመታት ተረጂ ሆኖ የመኖር እድል እንደሚገጠመው ነው ያወሱት።

በዚህም የህወሃት ቡድን የዚህ ዓይነቱን ቀውስ እየፈጠረ እንደሚሄድ ጠቅሰው፤ “የኢትዮጵያ መንግስትና የመከላከያ ሰራዊት እዳውን እንዲሸከምለት ያደርጋል” ብለዋል።

እንደርሳቸው ገለጻ፤ መንግስትና የእርዳታ ድርጅቶች እርዳታ እንዳያደርሱ፣ ለገበሬው ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ እንዳያቀርቡ እያሰናከለ፣ ህዝብ ተራበ ብሎ ራሱ ይጮሃል፤ ምክንያቱም ህወሃት መኖር የሚችለው የትግራይ ህዝብ ሲሞትና መከራ ሲያገኝ ብቻ ነው ማለታቸውም ተመላክቷል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img