Sunday, October 6, 2024
spot_img

በሱማሌ እና አፋር ክልል መካከል ያለው ግጭት በመባባሱ ምርጫ ለማካሄድ አስጊ ሆኗል ተባለ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ሰኔ 21፣ 2013 ― በሱማሌ እና አፋር ክልል ያለው የድንበር ይገባኛል ጥያቄ በመባባሱ ምርጫ ለማካሄድ ፈታኝ መሆኑ ተገልጧል፡፡

ተባብሶ ቀጥሏል የተባለው በሱማሌ እና አፋር ክልል ያለው የድንበር ይገባኛል ጥያቄ ሲሆን፣ በዚህም የዜጎች አለመረጋጋትና መፈናቀል በከፍተኛ ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱን የሱማሌ ክልል አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ መሐመድ ሮብሌ ተናግረዋል ብሎ አዲስ ማለዳ ጋዜጣ ዘግቧል።

በአፋር ክልል የሚገኙ ሚሊሻዎች የፈጠሩት የዜጎችን ሰላም የማወክ እና ማፈናቀል ተግባር ቀጥሏል ያሉት መሐመድ፣ የሱማሌ ክልል ተወላጆች የሚገኙባትን አዳይቱ የምትባለውን ቦታ ሙሉ በሙሉ በቁጥጥራቸው ስር ማድረጋቸውን ገልጸዋል። አፋር ክልል የሚገኙ ሚሊሻዎች ከተማዋን በማቃጠል በአካባቢው የሚገኘው ማኅበረሰብ እንዲሰደድ እና እንዲፈናቀል አድርገዋል ሲሉ አቶ መሐመድ ገልጸዋል።

የሱማሌ ተወላጆች የሚኖሩባት ይህች አዳይቱ የተባለችው ስፍራ በአፋር ክልል ሚሊሻዎች ተይዛ ነዋሪዎቹ ከባድ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ ነው አቶ መሐመድ የገለጹት።

በአሁኑ ሰዓት የአፋር ሚሊሻዎች ከተማዋን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥራቸው ስር ያደረጓት በመሆኑ፣ የነዋሪዎችን ደህንነት ለማስጠበቅ በጣም ከባድ እንደሆነባቸው ተናግረዋል። ‹‹በጣም አስቸጋሪ እና ከአቅማችን በላይ በመሆኑ ችግሩን ለማስቆም ተቸግረናል›› ሲሉ መሐመድ ገልጸዋል። ሰላም የሚፈልግ ማኅበረሰብ ቢኖርም በሁለቱም ክልሎች ተመሳሳይ ሰላም የሚፈልግ ማኅበረሰብ ባለመኖሩ፣ አንዱ ሰላም አፍራሽ አንዱ ሰላም ፈላጊ እየሆነ መምጣቱ ለችግሩ መባባስ ዋና ምክንያት ነው ብለዋል።

የመከላከያ ሠራዊት በአካባቢው ደርሶ ሰላም እንዲያሰፍን በተደጋጋሚ ጥሪ ብናቀርብም፣ በሦስት ቀን ውስጥ እንደርሳለን ብለውን የነበረ ቢሆንም፣ ዘግይተው መጥተው አልቻልንም የሚል ምላሽ ሰጥተውናል ብለዋል።

መሐመድ እንደሚሉት ከሆነ ‹‹በኛ በኩል በጣም ከብዶናል፤ መከላከያ ሠራዊትም ቢሆን ሚሊሻዎቹን ማስወጣት አልቻልንም ብሎናል›› ሲሉ ተናግረዋል።

የመከላከያ ሠራዊት መፍትሔ እናመጣለን ብሎን ነበር፣ ግን ምንም አይነት እርዳታ እያደረገ ስላልሆነ ነዋሪዎች በጣም ለከፋ ችግር እየተዳረጉ ነው ብለዋል። እንደ መሐመድ ገለጻ ከሆነ ሱማሌ ክልል ምርጫ የሚደረገው ጷጉሜ 1 ቢሆንም፣ አሁን ያለው ሁኔታ በጣም ከባድ በመሆኑ ምርጫ ለማካሄድ ስጋት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

በጉዳዩ ላይ የአፋር ክልላዊ መንግሥት ያለውን አስተያየት ለማካተት ጥረት አድርጌያለሁ ያለው ጋዜጣው፣ ነገር ግን ምላሽ ማግኘት እንዳልቻለ ገልጧል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img