አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ሰኔ 21፣ 2013 ― ከፌዴራል መንግሥት ጋር ጦርነት ውስጥ የሚገኙት የሕወሃት አመራሩ አቶ ጌታቸው ረዳ በትግራይ ገጠራማ ሥፍራ ከገበሬ ቤተሰብ ጋር እየኖሩ እንደሚገኙ የሚያመለክት ዘገባ ወጥቷል፡፡
ይህንኑ በመንግሥት የሚፈለጉትን አቶ ጌታቸው ረዳን በአካል ማግኘቷን በፎቶ ማስረጃ አስደግፋ ያወጣችው ለፊንላንድ ሚዲያ የምትሠራው ሊሴሎተ ሊንድስትሮም የተባለች ጋዜጠኛ ባሰናዳችው ዘገባ ተመላክቷል፡፡
ጋዜጠኛዋ ባጠናቀረችው ዘገባ፣ አቶ ጌታቸው በአሁኑ ወቅት ሥሙ ካልተጠቀሰ ሥፍራ ከገበሬ ቤተሰብ ጋር ሕይወት እየገፉ የሕወሃት ኃይሎችን እየመሩ መሆናቸው የሠፈረ ሲሆን፣ የሚመሩት የሕወሃት ኃይል ድጋፍ የሚያገኘው ከሕዝቡ እንደሆነም ተገልጧል፡፡
በዚሁ ዘገባ ላይ ጋዜጠኛዋ አቶ ጌታቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የኤርትራውን ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂን የሚመለከቱ ጉዳዮች ማንሳታቸው ተጠቅሷል፡፡
አቶ ጌታቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን በቀጠናው የፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂን ዐይነት አምባገነን የመሆን አላማ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
ወንጀለኛ አይደለንም ሲሉ መናገራቸው በዘገባው ላይ የተጠቀሰው የሕወሃት ኃይሎችን እየመሩ እንደሚገኙ የተነገረላቸው የቀድሞው የኢፌዴሪ መንግሥት የኮሚኒኬሽን ሚኒስትሩ፣ ወንጀለኛ ናችሁ የሚለን ካለ ግን በደስታ እናስተናግደዋለን ማለታቸውም ተመላክቷል፡፡
አክለውም አሁን እየተዋጉ የሚገኙበት ጦርነት የመጀመሪያ ዙር በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ የተናገሩ ሲሆን፣ ይህን አጠናቀው ወደ ቀጣዩ ዙር እንደሚሸጋገሩም ገልጸዋል፡፡
አቶ ጌታቸው የሚዋጉት ለትግራይ መሆኑን በመናገርም፣ የሚፋለሙለት አላማ ሞትን አስፈሪ እንደማያደርግባቸውም አስረድተዋል፡፡
ከዘገባው ቀድሞ በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች የተሰራጨው የአቶ ጌታቸው ረዳ እና የጋዜጠኛዋ ሊሴሎተ ሊንድስትሮም ፎቶ በሥፋት መነጋጋሪያ እንደሆነ ቀጥሏል፡፡