Friday, November 22, 2024
spot_img

የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልሎች መካከል ጣልቃ እንዲገባ ሥልጣን የሚሰጠው ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ ቀረበ

አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ሰኔ 19፣ 2013 ― የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሁለት ክልሎች ወይም በፌዴራልና በክልሎች መካከል የሚነሱ አለመግባባቶችን ለመፍታት፣ ክልሎች ካልጠየቁና ችግሩ ከቀጠለ፣ ምክር ቤቱ በራሱ ተነሳሽነት መፍትሔ እንዲፈልግ የሚፈቅድ አሠራር የያዘ ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ ቀረበ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዓርብ ሰኔ 18፣ 2013 በዋለው ሦስተኛ ልዩ ስብሰባው፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለማጠናከርና ሥልጣንና ተግባሩን ለመዘርዘር የወጣውንና 20 ዓመታት ያስቆጠረውን አዋጅ ቁጥር 251/1993 ለማሻሻል በቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቷል፡፡

የተሻሻለው ረቂቅ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አሁን እየቀረቡ ካሉ የሕዝብ ፍላጎቶችና ጥያቄዎች አንፃር፣ በሕገ መንግሥቱ የተሰጡትን ተልዕኮዎች በቀልጣፋና በውጤታማ መንገድ ለመፈጸም በሚያስችለው ቁመና ላይ አለመገኘቱን ያስረዳል፡፡

አሁን በሥራ ላይ ያለው አዋጅ በክልሎች መካከል ወይም በፌዴራልና በክልል መንግሥታት መካከል የሚነሱ አለመግባባቶችንና ሁለቱ ወገኖች ግጭት ውስጥ ከገቡ፣ በውይይት እንዲፈታ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሁኔታዎችን እንዲያመቻች ይደነግጋል፡፡ ሁለቱ ወገኖች ካልተስማሙ በአንደኛው ወይም በሁለቱም ወገኖች በሚቀርብ ጥያቄ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ምክር ቤቱ ችግሩ ዕልባት እንዲያገኝም ይደነግጋል፡፡

ይሁን እንጂ ከዚህ ቀደም በተግባር የታየው በሁለት ወገኖች መካከል የሚያወዛግብ ጉዳይ እንዳለ እየታወቀ፣ አንዱ ወይም ሁለቱ ወገኖች ጥያቄ ባለማቅረባቸው ምክንያት ብቻ ምክር ቤቱ የመፍትሔ ዕርምጃ ሳይወስድ መቆየቱን ለውይይት የቀረበው ረቂቅ ሰነድ ያስረዳል፡፡

በሌላ በኩል አሁን በሥራ ላይ ባለው ሕግ የራስን ዕድል በራስ ከመወሰን መብት ጋር ተያይዞ ጥያቄ ከቀረበ በኋላ፣ ምክር ቤቱ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ይወስናል በሚል የሚደነግግ ሲሆን፣ ከዚህ ውጪ አቤቱታ ከቀረበና ከውሳኔ በፊት ምክር ቤቱ ምን ምን ተግባራትን ማከናወን እንዳለበት ባለመገለጹ፣ በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ጥያቄ ላይ ውሳኔ ከመሰጠቱ በፊት ጥናት የማድረግና የሕዝብን ፍላጎት የመጠየቅ የመሳሰሉ ቁልፍ ተግባራት እንዲያከናውን የሚል አንቀጽ ተቀምጧል፡፡

እንዲሁም በአንድ ክልል የቀረበ የማንነት ጥያቄ ታይቶ ለክልሉ ጥያቄው ተገቢ አይደለም ተብሎ ውሳኔ ከተሰጠበት በኋላ፣ ውሳኔውን የሚያስለውጡ ሁኔታዎች ቢፈጠሩና በድጋሚ በማየት የተለየ ውሳኔ ለመስጠት ቢወሰን፣ ለዚሁ አሠራር ቦታ የሚሰጥ ረቂቅ እንደሆነም ተመልክቷል፡፡

በሌላ በኩል የምርጫ ክልልን በተመለከተ አሁን በሥራ ላይ ያለው አዋጅ የምርጫ አከላለልን አስመልክቶ ምክር ቤቱ የሚቀርብለትን የውሳኔ ሐሳብ መርምሮ እንዲያፀድቅ የሚቀርብ ሲሆን፣ ምርጫ ቦርድ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ የውሳኔ ሐሳብ ማቅረብ እንዳለበት አለመገለጹ ተጠቁሟል፡፡

በመሆኑም በረቂቅ አዋጁ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አጠቃላይ አገራዊ ምርጫ ከመካሄዱ አንድ ዓመት በፊት፣ የምርጫ ክልሎችን አከላለል ረቂቅ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የውሳኔ ሐሳብ ማቅረብ እንዳለበት ግዴታ የሚጥል ድንጋጌም ተጨምሯል፡፡

ጀምበር አስማማው የተባሉ የምክር ቤቱ አባል፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልሎች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን እንዲፈታ የነበረውን አሠራር ከዚህ ቀደም ያልተጠቀመበት በመሆኑ፣ አሁንም በቀጣይ ጊዜያት ተጨምረው የመጡት የረቂቅ አዋጁ ክፍሎች በሚገባ ታይተው ሚናው መለየት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

በመጨረሻም ረቂቅ አዋጁ ለተጨማሪ ዕይታ ለሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል መባሉን የዘገበው ሪፖርተር ነው።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img