– ሕወሃት የጦር አውሮፕላኑን መትቶ መጣሉን እየገለጸ ይገኛል
አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ሰኔ 18፣ 2013 ― ባለፈው ረቡዕ ትግራይ ክልል ውስጥ አንድ ወታደራዊ አውሮፕላን ባጋጠመው የቴክኒክ ችግር ምክንያት መውደቁን የአገር መከላከያ ሠራዊት ቃል አቀባይ ገልጸዋል፡፡
ሆኖም ከመከላከያ ጋር እየተፋለመ ነው የሚባለው ሕወሓት ግን፣ የጦር መሳሪያና የኤርትራ ሠራዊትን የደንብ ልብስ የለበሱ ወታደሮችን የጫነ ነው ያለውን አውሮፕላን፣ ኃይሎቹ መትተው መጣላቸውን ገልጧል፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ቃል አቀባይ ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ነግረውኛል ብሎ ቢቢሲ እንደዘገበው፣ አውሮፕላኑ የወደቀው ባጋጠመው የቴክኒክ ችግር ምክንያት ነው፡፡
የአገር መከላከያ ቃል አቀባዩ ‹‹በሌሎችም አውሮፕላኖች ላይ እንደሚያጋጥመው ሁሉ አውሮፕላኑ በቴክኒክ ችግር ምክንያት ነው የወደቀው›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ጨምረውም ከወደቀው አውሮፕላን ጋር በተያያዘ የደረሰ ጉዳት ካለ በቅርቡ እንደሚገለጽ በመጥቀስ፣ ዝርዝር ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ሔርኩለስ ሲ-130 የተባለው የማጓጓዣ አውሮፕላን፣ ወድቆበታል ከተባለ ሥፍራ የአውሮፕላኑ ስብርባሪ ነው የተባለ ምስል በሕወሃት አመራሩ ጌታቸው ረዳ ከሰሞኑ በትዊተር ተጋርቶ ነበር።
ቢቢሲ የአውሮፕላኑን ስብርባሪ የያዙ ፎቶ ግራፎችን እና ቪዲዮዎችን መመርመሩን ያሳወቀ ሲሆን፤ በቪዲዮው ላይ የሚነጋገሩ ሰዎች እንደሚሉት ቦታው ከመቐለ ደቡብ ምዕራብ 25 ኪሎ ሜትሮችን ርቃ የምትገኘው አዲ ቃአላ እንደሆነች እንደሚያመለክት አሳውቋል፡፡
ነገር ግን በአውሮፕላኑ ውስጥ ምን ያህል ሰዎች እንደነበሩ የተገለጸ ነገር የለም።
በሌላ በኩል ባለፈው ሳምንት በትግራይ ክልል ውስጥ የተጠናከረ ውጊያ መካሄዱ የተነገረ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ አየር ኃይል በገበያ ቦታ ላይ ጥቃት ፈጽሞ በርካታ ሠላማዊ ሰዎችን ገድሏል እንዲሁም አቁስሏል በሚል ተከሷል።
ነገር ግን ሠራዊቱ ጥቃቱም በገበያ ቦታ ላይ ሳይሆን፣ ኢላማ ያደረገው የሕወሃት ኃይሎች ላይ መሆኑን በመግለጽ ክሱን ውድቅ አድርጎታል።
በዚህ ጥቃት በትንሹ 43 ሰዎች እንደተገደሉ ሬውተርስ ዘግቧል፡፡