Monday, November 25, 2024
spot_img

የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ኅብረት ለምርጫ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት ይፋ አደረገ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ሰኔ 17፣ 2013 ― በስድስተኛው አገራዊና ክልላዊ ምርጫ የሲቪል ማኅበራትን ተሳታፊነት ለማረጋገጥ በሚል 176 ማኅበራት በጋራ በመሆን የመሠረቱት የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራት ኅብረት ለምርጫ የተሰኘው ቡድን ባሳለፍነው ሰኞ የተካሄደውን ምርጫ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት ይፋ አድርጓል፡፡

ኅብረቱ ባወጣው ሪፖርት ትዝብት ከተደረገባቸው 93 በመቶ በሚሆኑ ምርጫ ጣቢያዎች ላይ የምርጫ ጣቢያ አስፈፃሚዎች የኅብረቱ ታዛቢዎች በጣብያው ሲደርሱ በሥፍራው መገኘታቸውን ማረጋገጡን ገልጧል፡፡

ሪፖርቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሰጠውን የታዛቢነት ማረጋገጫ ባጆችን ያቀረቡ 97 በመቶ በሚሆኑ የምርጫ ጣቢያዎች የሚሆኑ ታዛቢዎቻችን ወደ ምርጫ ጣቢያ በመግባት እንዲታዘቡ ተፈቅዶላቸዋል ያለ ሲሆን፣ የድምፅ መስጫ ጣቢያ አከፋፈት ስርዓትን በተመለከተ
ታዛቢዎች ከላኳቸው ሪፖርቶች 98 በመቶ የሚሆኑት የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች ከጠዋቱ 1 ሰዓት በፊት መከፈታቸውን አመልክቷል፡፡

በምርጫ ህጉ ከተደነገገው በተቃራኒ 4 በመቶ የሚሆኑት የኅብረቱ ታዛቢዎች የታዘቧቸው ጣቢያዎች ህጉ በከለከላቸው ስፍራዎች ማለትም ፖሊስ ጣቢያዎች፣ ወታደራዊ ካምፖች እና የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚገኙባቸው ህንፃዎች ውስጥ መከፈታቸውን ታዛቢዎች ሪፖርት ማድረጋቸውን ጠቅሷል፡፡

በሌላ በኩል ምርጫ ህጉ በተደነገገው መሰረት ከድምፅ መስጫ ቀን በፊት ባሉት አራት (4) ቀናት የምርጫ ቅስቀሳ ማካሄድ እንዲሁም ከድምፅ መስጫ ጣብያው በ200 ሜትር ርቀት የምርጫ ቅስቀሳ ቁሳቁስ መታየት በግልፅ ቢከለከልም፣ ኅብረቱ ካሰማራቸው ታዛቢዎች 12 በመቶ የሚሆኑት ሰኔ 14፣ 2013 በድምፅ መስጫ ጣብያዎች አቅራቢያ ቅስቀሳ መደረጉን ወይም የቅስቀሳ ቁሳቁስ መታየቱን ሪፖርት አድርገዋል።

ኅብረቱ ከታዘባቸው የምርጫ ጣቢይዎች 96 በመቶ (ማለትም 2,020 በሚሆኑ የምርጫ ጣቢያዎች) የሚሆኑት በድምፅ አሰጣጥ ወቅት እንዲገኙ የተፈቀደላቸው አካላት ብቻ ተገኝተዋል ብለው ሪፖርት ያደረጉ ሲሆን፣ በአንፃሩ በ86 ክስተቶች በምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ እንዲገኙ ያልተፈቀደላቸው ሰዎች መኖራቸውን ታዛቢዎች ገልጸዋል፡፡

የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ መመርያ ባከበረ መልኩ በ95 በመቶ (ማለትም 1,983 በሚሆኑ የምርጫ ጣቢያዎች) ያህሉ ታዛቢዎች በተገኙባቸው ጣቢያዎች የድምፅ ቆጠራ ሂደቱን እንዲታዘቡ ተፈቅዶላቸው ነበር ያለው ኅብረቱ፣ ከታዘባቸው የምርጫ ጣቢያዎች በ99 በመቶ (ማለትም 2,043 በሚሆኑ የምርጫ ጣቢያዎች) ያህሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የድምፅ መስጫ ወረቀቶች በጣቢያው የተቆጠሩ ሲሆን፣ በ93 በመቶ (ማለትም 1,927 በሚሆኑ የምርጫ ጣቢያዎች)ያህሉ የክልል እና የከተማ አስተዳደር ምክር ቤቶች የድምፅ መስጫ ወረቀቶች በጣቢያው ቆጠራዎች መካሄዳቸውን እንደታዘቡ አመላክቷል፡፡

ኅብረቱ በዚህ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት በድምፅ መስጫው ዕለት ከታዩት አሳሳቢ ኩነቶች መካከል የምርጫ ቁሳቁሶች መጓደል፣ ታዛቢዎች እንዲታዘቡ ያለመፍቀድ፣ በምርጫ ጣቢያው ውስጥ እንዲገኙ ያልተፈቀደላቸው ሰዎች መገኘት እና በድምጽ አሰጣጥ እና በመቁጠር ወቅት ማስፈራራት እና ትንኮሳዎችን ዘርዝሯል፡፡

በኦሮምያ ክልል የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አስተባባሪዎች ከቦርዱ ዕውቅና የተሰጣቸው ታዛቢዎች ዝርዝር ሊደርሰን ይገባል በሚል እምነት የመታዘቢያ ባጅ የያዙ የሕብረቱ ታዛቢዎች እንዳይታዘቡ ክልከላ ተደርጎባቸዋል ብሏል፡፡

በተጨማሪም የሕብረቱ ታዛቢዎች በምርጫ ጣቢያዎቹ ውስጥ እንዲገኙ ያልተፈቀደላቸው ሰዎች መገኘታቸውን የሚያስረዱ 30 ሪፖርቶች አድርገዋል ያለ ሲሆን፣ ለአብነት በአማራ ክልል የተሰማሩ የሕብረቱ ታዛቢዎች በተለይም በአንዳንድ አካባቢዎች ሊቀመንበሩን ጨምሮ የቀበሌ ሰራተኞች በድምጽ መስጫ ወቅት በጣቢያዎች ውስጥ እንደተገኙ ጠቁሟል፡፡

የሕብረቱ ታዛቢዎች በ17 የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ ማዋከብን እና ማስፈራራት መመልከታቸውን ሪፖርት አድርገዋል። በተወሰኑ የጋምቤላ እና የአማራ ክልሎች አካባቢዎች የፖለቲካ ፓርቲ አባላት በድምጽ መስጠት ወቅት መራጮችን እና የምርጫ አስፈፃሚዎችን ሲያስጭንቁ እና ሲያስፈራሩ እንደነበር ታዛቢዎች ሪፖርት ማድረጋቸውንም ይፋ አድርጓል፡፡

የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ኅብረት ለምርጫ በማጠቃለያው ከነዚህ ጉድለቶች ወውጭ ምርጫው ሠላማዊ ሆኖ ማለፉን አስታውቋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img