Saturday, October 12, 2024
spot_img

ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ከሱዳን ጋር ያለው ችግር በንግግር ይፈታል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናገሩ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ሰኔ 17፣ 2013 ― ከጎረቤት አገር ሱዳን ጋር ያለው ወቅታዊ ችግር በንግግር ይፈታል የሚል እምነት እንዳላቸው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን የተናገሩት፣ ባለፈው ሳምንት ዐርብ በገዢው ፓርቲ ንብረት ‹ፋና› ሊተላለፍ ቀጠሮ ተይዞለት ወቅቱ የምርጫ ጥሞና በመሆኑ በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን እንዳይተላለፍ በተከለከለውና ትላንት ምሽት በተለያዩ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ለአየር በበቃው ቃለ ምልልስ ነው፡፡

በዚሁ ቃለ ምልልስ የሱዳንን ሕዝብ ‹‹የሚወደንና የምንወደው ወንድም ሕዝብ›› ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ብዙ መከራ እና ችግር በጋራ ስላሳለፍን› ያለውን ችግር ‹‹በንግግር ይፈታል›› የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

ባለፈው ጥቅምት ወር የተቀሰቀሰውን የፌዴራል መንግሥት እና የሕወሃት ኃይሎች ጦርነት ተከትሎ የሱዳን ጦር ወደ ኢትዮጵያ ድንበር በመጠጋቱ የተፈጠረው የኢትዮጵያ እና የሱዳን የድንበር ውዝግብ ያለ መፍትሔ ወራትን አስቆጥሯል፡፡

ሁለቱ አገራት 750 ኪሎ ሜትሮች ያህል የጋራ ድንበር ሲኖራቸው፣ ከዚህ ቀደምም ለዓመታት በድንበር አካባቢ ግጭት ሲያጋጥም ቆይቷል፡፡ በተለይ አል ፋሽቃ በሚባለው ለም የእርሻ መሬት ባለበት አካባቢ ግጭቶች በተለያዩ ጊዜያት መከሰታቸው ይነገራል።

በድንበር አካካቢ ተከስቶ ወራትን ያስቆጠረው ውጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ሲሆን፣ በሠላማዊ ሰዎችና በወታደሮች ላይ ጉዳት መድረሱ እንዲሁም በሺሕዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ለመፈናቀል ተዳርገዋል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img