Sunday, October 6, 2024
spot_img

ኦፌኮ የጋራ መንግሥት እንዲቋቋም ጠየቀ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ሰኔ 17፣ 2013 ― የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ‹‹በአስቸኳይ ሁሉን አካታች የጋራ መንግሥት እንዲቋቋም›› ወቅታዊ ፖለቲካዊ ሁኔታዎችን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ጠይቋል፡፡

‹‹በብሔራዊ መግባባት ያልታጀበ ምርጫ ሀገሪቱን ከገባችበት የፖለቲካ ቅርቃር እንደማያወጣት ደጋግመን አስገንዝበናል›› ያለው ኦፌኮ፣ ‹‹በአንድ ፓርቲ የበላይነት›› ተጠምዷል ያለው ገዢው ፓርቲ፣ የውይይት ጥያቄውን ሁሉ ‹‹ወደ ደንቆሮ ውይይት›› ቀይሮታል ሲል ቀድሞ ተፈጥሯል ያለውን ሁኔታ አስታውሷል፡፡

ፓርቲው ተገፍቼ ወጥቼበታለሁ ባለውና ‹‹ቴአትር›› ሲል በገለጸው ሰኞ እለት የተካሄደው ምርጫ፣ ‹‹መላውን የኢትዮጵያ ሕዝቦችን የማይወክል›› ነው ብሎታል፡፡

ኦፌኮ በመግለጫው ከሦስት ዓመታት በፊት በኦሮሞ ወጣቶች ደም ተገኝቷል ላለው ‹‹ለውጥ››፣ በዋናነት ወጣቶቹ ይደግፏቸዋል ያላቸው ድርጅቶቸ ማለትም ራሱ ኦፌኮ እና ኦነግ ከምርጫው ውጭ በመሆናቸው፣ ‹‹በኦሮሞ ሕዝብ የነፃነት ትግል ታሪክ ውስጥ አንድ ትልቅ ጥቁር ነጥብ›› ነው ያለ ሲሆን፣ ለመብት ትግሉም ‹‹ዳግመኛ ክህደት ይመስለናል›› ሲል አስፍሯል፡፡

ምርጫውንም ‹‹በምንም ተአምር የሀገራችንን ፍላጎቶች የማያሟላ›› ነው ያለው ፓርቲው፣ መፍትሔ ያመጣሉ ያላቸውን ሐሳቦች አስቀምጧል፡፡

ፓርቲው መፍትሔ ይሆናሉ ካላቸው መካከል ‹‹በአስቸኳይ ሁሉን አካታች የጋራ መንግስት እንዲቋቋምና ያልተሳካውን የመንግስት ተቋማት ተሃድሶ እንዲቀጥል፣ በአስቸኳይ ሁሉን አካታች ብሔራዊ የመግባባት ድርድር እንዲጀመር›› እንዲሁም ‹‹የጋራ መንግስቱ በጋራ የሚፈጥር ፍኖተ ካርታ እንዲመቻችና በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሁሉን አቀፍ፣ ነፃ ፍትሐዊና ተቀባይነት ያለው ምርጫ እንዲካሄድ›› የሚሉት ይገኙበታል፡፡

የኦሮሞ ፌሴራላዊ ኮንግረስ፣ ‹‹ታሪካዊ›› ባለው በዚህ ወቅት ‹‹ሁሉም ለአገራችን ቅን እና ገንቢ አሳቢ የሆናችሁ መላው ኢትዮጵያዊያንና ዓለም አቀፍ ኅብረተሰብ›› ከጎናችን በመቆም፣ በአገሪቱ ዘላቂ ሠላምና ዴሞክራሲያዊ ሽግግር እንዲከወን አግዙን ሲል ጥሪውን አቅርቧል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img