Saturday, October 12, 2024
spot_img

በትግራይ ክልል ውስጥ ከባድ ውጊያ መካሄዱ ተነገረ

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ሰኔ 16፣ 2013 ― በትግራይ ክልል በሚገኙ በርካታ አካባቢዎች ውስጥ በአገር መንግሥቱ ሠራዊትና በአማጺው ሕወሃት ኃይል መካከል ከባድ ውጊያዎች እየተካሄዱ መሆናቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

ራሱን የትግራይ መከላከያ ኃይል ብሎ የሚጠራው የሕወሀት ኃይል በርካታ የክልሉን ከተሞችን መያዙን የገለጸ ሲሆን፣ ተዋጊዎቹ በአካባቢያቸው ሲንቀሳቀሱ ማየታቸውን የዜና ተቋሙ የዐይን እማኞች ነግረውኛል ብሏል፡፡

የአገር መከላከያ ሠራዊት ግን ቡድኑ አገኘሁ ያለውን ድል ሐሰተኛ ዜና ሲል አጣጥሎታል።

ባለፈው ጥቅምት ወር የተቀሰቀሰው ውጊያ በሳምንታት ጊዜ ውስጥ በድል መጠናቀቁን የፌዴራል መንግሥት ካሳወቀ በኋላ የአሁኑ ውጊያ እጅግ ከባዱ መሆኑ ተነግሯል።

የሕወሃት ቡድን ቃል አቀባይ ነው የተባለ ገብረ ገብረ ጻድቅ እንደተናገረው በርካታ ከተሞችን ኢላማ በማድረግ ጥቃት መፈጸም የጀመሩት ባለፈው ሳምንት ሲሆን፣ በዚህም ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችን ማውደማቸውንና ወታደሮችን መማረካቸውን ገልጿል።

የሕወሃት ቡድን ከኤርትራ ድንበር በ45 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ወደምትገኘው አዲግራት ከተማ መግባታቸውም የተነገረ ሲሆን፣ ትላንት ቀትር ላይ ተመልሰው ወጥተዋል ተብሏል፡፡ አማጺው ቡድን ይህን ያደረገው የገባበው አላማ አቅርቦት ለመሰብሰብ ነው የሚሉ መረጃዎች ወጥተዋል፡፡

የሕወሃት ተዋጊዎች ከክልሉ መቀመጫ መቀሌ ዙሪያ እንዲሁም በሰሜንና በደቡብ ባሉ የክልሉ አካባቢዎች በሚገኙ በርካታ ስፍራዎች ላይ መታየታቸውም ተነግሯል።

የአገር መከላከያ ሠራዊት ቃል አቀባይ የሆኑት ኮሎኔል ጌትነት ከባድ ውጊያ እንደነበረ አረጋግጠው፤ አማጺያኑ ከተሞችን፣ የጦር መሳሪያዎችን ወይም ወታደሮችን ማርከናል ያሉትን ሐሰት ነው ሲሉ አጣጥለውታል።

ኮሎኔሉ ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት ምርጫ በማካሄድና በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ሥራ በበዛበት ጊዜ ሽብርኛው ህወሓት፣ ታዳጊዎችን በማሰለፍ በሽብር ተግባራት ላይ ተሰማርቶ ነበር›› ብለዋል፡፡

የተካሄደው ዘመቻ የአማጺውን ቡድን መሪዎች ለመያዝ እንደነበርም ገልጸዋል፡፡

በአገር መከላከያ ሠራዊት እና ሕወሃት መካከል የሚካሄደው ውጊያ ከተቀሰቀሰ ስመንት ወራት ሊደፍን ቀናት ቀርተውታል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img