አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ሰኔ 15፣ 2013 ― ከፌዴራል መንግሥት ጋር ጦርነት ውስጥ የሚገኙት የሕወሃት አመራሩ አቶ ጌታቸው ረዳ፣ የሚመሩት የሕወሃት ኃይል ማርኳቸዋል ያላቸውን የአገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ቀልቡልን ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ላይ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አቶ ጌታቸው ረዳ ማርከናቸዋል ላሏቸው የሠራዊት አባላት ቀለብ እንዲያቀርቡ የጠየቁት ለዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር እና ለረድኤት ድርጅቶች ነው፡፡
አቶ ጌታቸው ከዚህ ጥሪ ጋር አያይዘው ባሠራጩት ተንቀሳቃሸ ምስል የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላትን መለዩ የለበሱ ሰዎች በሰልፍ ሲጓዙ ይታያል፡፡ እነዚህ መለዮ ለባሾች የተቀረፁት በየትኛው የትግራይ አካባቢ እንደሆነ የተገለጸ ነገር የለም፡፡
በዚሁ ተንቀሳቃሽ ምስል ውስጥ አንድ በአማርኛ ቋንቋ ‹‹አይዟችሁ ውጊያው አልቋል፣ እዚህ እየተኮሱ ነው፣ እየተለማመዱ›› የሚል ድምጽ የሚሰማ ሲሆን፣ ሌላ በትግርኛ ቋንቋ የምትናገር ሴት ድምጽም ይሰማል፡፡
በመንግስት የሚፈለጉት የሕወሃት አመራር ስላጋሩት ተንቀሳቃሽ ምስል ከአገር መከላከያ ሠራዊት የተሰጠ ምላሽ የለም፡፡
በሕወሃት ኃይሎች እና በፌደራል መንግስት መካከል የሚካሄደው ጦርነት ከጀመረ 8 ወራት ሊደፍን 10 ቀናት ቀርተውታል፡፡