አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ሰኔ 15፣ 2013 ― በትላንትናው እለት በተካሄደው ምርጫ በግል እጩነት የቀረቡት የእስልምና መምህሩ ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ እና ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በተወዳደሩባቸው የምርጫ ቦታዎች እየመሩ መሆናቸውን እየወጡ የሚገኙ የምርጫ ውጤቶች አመልክተዋል፡፡
ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ የተወዳደሩት በኦሮሚያ ክልል፣ በኢሉ አባቦራ ዞን፣ በመቱ ወረዳ ለሕዝብ ተወካዮች ወንበር ሲሆን፣ በምርጫ ክልሉ ከተወዳደረው ገዢው የብልጽግና ፓርቲ እጩ የላቀ ውጤት ማግኘታቸውን አምባ ዲጂታል የደረሰው መረጃ ያመለክታል።
በአዲስ አበባ ከተማ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ በብቸኝነት እጩ ባላቀረበበት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወንበር የተወዳደሩት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት እስከአሁን በወጡት የምርጫ ጣቢያዎች ውጤት መሰረት ሳያሸንፉ እንዳልቀረ ተዘግቧል።
በትላንትናው እለት በሰባት ክልሎች የተካሄደው ምርጫ አጠቃላይ ውጤት በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ የሚደረግ መሆኑ ይታወቃል።