አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ሰኔ 15፣ 2013 ― የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሲዳማ ክልል ሲካሄድ የነበረው ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ በትላትናው እለት በመቋረጡ ምክንያት ዛሬ ረፋድ 5 ሰአት ላይ እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡
የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ትላንት ምሽት ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት በክልሉ ከድምጽ መስጫ ወረቀቶች እጥረት ጋር በተያያዘ የድምጽ መስጠት ሂደቱ ተቋርጧል፡፡
ይህ ሆነው ‹‹የድምጽ መስጫ ወረቀቶች በ100 መታሸግ ሲኖርባቸው በ50 በመታሸጋቸው፤ በ19 ምርጫ ክልሎች [ሁሉም ምርጫ ክልሎች] ላይ የድምጽ መስጫ ወረቀቶች በግማሽ ጎድሏል›› ያሉት ብርቱካን፤ የድምጽ መስጠት ሂደቱን በታቀደለት ቀን ትላንት ማጠናቀቅ ስለማይቻል ዛሬ ‹‹ከቀኑ 5 ሰዓት ጀምሮ በሲዳማ የምርጫ ክልሎች ሁሉ ሂደቱ ይቀጥላል›› ብለዋል።
በትላንትናው እለት በሰባት ክልሎች የተካሄደው ስድስተኛው ምርጫ በአብዛኛው በሰላማዊ መንገድ መጠናቀቁን ምርጫ ቦርድ ምሽት ላይ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ከ37 ሚሊዮን በላይ መራጮች በተመዘገቡበት እና 47 የፖለቲካ ፓርቲዎች የተፎካከሩበት ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ትላንት ከምሽቱ 3፡00 መጠናቀቁን አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ለሐዝቡ አስተላልፈዋል።
የድምጽ መስጠት ሒደት ተጠናቆ ቆጠራ ያደረጉ የምርጫ ጣቢያዎቸ ውጤት እየለጠፉ እንደሚገኙ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ዘግቧል፡፡