Friday, October 11, 2024
spot_img

ከሥርጭት ታግዳ ነበር የተባለችው “ፍትሕ” መጽሔት ነገ ለንባብ ልትበቃ ነው

አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ሰኔ 12፣ 2013 ― በየሳምንቱ ቅዳሜ ለንባብ የምትበቃው “ፍትሕ” መጽሔት በነገው እለት ለሥርጭት ልትበቃ መሆኑን ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ድረገጽ ዘግቧል።

ጉዳዩን በተመለከተ የ“ፍትሕ” መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ተመስገን ደሳለኝ፤ ዛሬ ስለተከሰተው ሁኔታ የትኛውም የመንግስትም ሆነ የጸጥታ አካል አስቀድሞ እንዳላነጋገራቸው ገልጸዋል። ጉዳዩን የሰሙትም በስልክ እንደሆነ ጠቁመዋል።

“ማንም ያነጋገረን፣ የመጣ ህጋዊ ሰው የለም። ከማገዳቸው በፊት ‘ከምርጫ ጋር ግንኙነት ያለው ነገር አለው ወይ? ብለው ቢጠይቁን ማብራሪያ እንሰጣቸው ነበር። እኛን ሳያነጋግሩ ፖሊስ ልከው ማተሚያ ቤቱን ከብበው ነው እንዳይወጡ ያደረጉት” ሲሉ አስረድተዋል።

መጽሔቷ በዛሬው ዕለት ለገበያ ሊቀርብ የነበረው ዕትሟ የሽፋን ገጽ የአዲስ አበባ ጉዳይን የሚመለከት ነበር።

“ለአዲስ አበባ አይሆኑም” በሚል በትምህርተ ጥቅስ ውስጥ የሰፈረ ርዕስ የተሰጠው ይሄው የመጽሔት ሽፋን፤ በተመስገን ደሳለኝ የተጻፈን ጹሁፍ የሚያስተዋውቅ ነው። ለጹሁፉ የመረጠውን ርዕስ የተዋሰው ሰሞኑን በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ሲዘዋወር ከነበረ ሃሳብ መሆኑንም የጠቆመው ተመስገን፤ አንባቢዎቹ “አዲስ አበባን ማን ይታደጋት?” የሚለውን ጥያቄ እያሰላሰሉ ጽሁፉን ያነብቡ ዘንድ ይጋብዛል።

መጽሔቷን እግድ ተከትሎ አታሚው የ“ኢትዮ ከለር አታሚዎች” ቅጽር ግቢን ለሰዓታት ሲጠብቁ የቆዩት የፖሊስ አባላት፤ ስለ መጽሔቱ መረጃ የደረሳቸው ከትላንት ምሽት አራት ሰዓት ጀምሮ እንደው ሲናገሩ መደመጣቸውን የመጽሔቷ አዘጋጆች ተናግረዋል። የመጽሔቱ ስርጭት ከመሸ በኋላ ይከናወናል በሚል ስጋትም አካባቢውን ለሊቱን ሙሉ ሲጠብቁ ማደራቸውን መናገራቸውንም ጠቅሰዋል።

ፖሊሶቹ የመጽሔቷን ኮፒ “የበላይ አካላት” ላሏቸው ግለሰቦች መውሰዳቸውን የሚናገሩት አዘጋጆቹ፤ ከግለሰቦቹ ምላሽ ካገኙ በኋላ መጽሔቱ መሰራጨት እንደሚችል ለማተሚያ ቤቱ ሰዎች መናገራቸውን አብራርተዋል። “ ፖሊሶቹ ‘የበላይ አካል አንብቦ ቢወጣ ችግር አይፈጥርም’ ብለዋል” ሲሉ የመጽሔቷ አንድ አዘጋጅ ተናግረዋል።

ከዛሬ ንጋት ጀምሮ እስከ ቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ገደማ የቆየው የ“ፍትሕ” መጽሔት ስርጭት እግድ መቆሙን የተረዱት አዘጋጆች እና የስርጭት ባለሙያዎች፤ የመጽሔቷን 137ኛ ዕትም በነገው ዕለት ለንባብ እንደሚያበቁ አስታውቀዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አባላት የ“ፍትሕ” መጽሔትን እንዳይሰራጩ አድርገዋል መባሉን በተመለከተ ጥያቄ የቀረበላቸው የከማይቱ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ፤ “ስለ ጉዳዩ መረጃ የለኝም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። “እንዴት ተከለከለ፣ እንዴት ተፈቀደ የሚለውን አላውቀውም” ሲሉ ኮማንደር ፋሲካ ተናግረዋል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img