አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ሰኔ 12፣ 2013 ― የአውሮፓ ኅብረት በመጪው ሰኞ ሰኔ 14 ለሚካሄደው አገራዊ ምርጫ ታዛቢ መላክ ባለመቻሉ እንደሚያዝን በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ ለይ አስታውቋል፡፡
ኅብረቱ ከወር በፊት ምርጫውን ለመታዘብ ያስችሉኛል ባላቸው ሁኔታዎች ዙሪያ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ባደረገው ውይይት አለመስማማቱን በመግለጽ፣ የመታዘብ እቅዱን እንደተወ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ የአውሮፓ ኅብረት ምርጫውን ለታዘብ ያስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች ‹‹ሉዓላዊነት ስለሚጋፉ›› በሚል ኅብረቱ ምርጫ ለመታዘብ ያስቀመጣቸውን ቅድመ ሁኔታ እንደማይቀበል አስታውቆ ነበር፡፡
ኋላም የኢትዮጵያ መንግሥት አቋሙን መሳወቁን ተከትሎ ኅብረቱ በምርጫው እለት ልኡክ እንደሚልክ የገለጸ ቢሆንም፣ ዛሬ በወጣው መግለጫ ግን በድጋሚ ምርጫውን የሚታዘብ ልዑክ መላክ እንደማይችል በማሳወቅ በድርጊቱ ማዘኑን ገልጿል።
ሆኖም ሰኞ የሚካሄደው ምርጫ ለኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ለውጥ ሂደት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው የገለጸው የአውሮፓ ኅብረት፣ ምርጫ ቦርድ አከናውኗቸዋል ላላቸው ሥራዎች ከዚህ ቀደም ድጋፍ ማድረጉን እንዲሁም እውቅና እንደሚሰጥና በቀጣይ ከኢትዮጵያ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ አብሮ እንደሚሠራ አስታውቋል።
በተጨማሪም በምርጫው ወቅት ሁሉም አካላት የጥላቻ ንግግሮችን ከመሰንዘር አንዲሁም ወደ ግጭት የሚመሩ ተግባራትን ከመፈጸም እንዲቆጠቡ አሳስቧል፡፡
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የሰብዓዊ መብት ጥሰት፤ የፖለቲካ ውጥረቶች እና ሌሎች ውስብስብ ችግሮች አሉባት ያለው የህብረቱ መግለጫ፣ በቀጣይ ሁሉን አቀፍ ውይይቶች በአገሪቱ እንዲደረጉም ጠይቋል፡፡