Tuesday, October 8, 2024
spot_img

የአውሮፓ ኅብረት ልዩ መልእክተኛው ፔካ ሐቪስቶ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ‹‹የትግራይን ሕዝብ እናጠፋዋለን›› ብለው እንደነገሯቸው ተናገሩ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ሰኔ 11፣ 2013 ― የፊንላንዱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር እና የአውሮፓ ኅብረት ልዩ መልእክተኛው ፔካ ሐቪስቶ በትላንትናው እለት የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ‹‹የትግራይን ሕዝብ እናጠፋዋለን›› ብለው እንደነገሯቸው ለአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት ተናግረዋል፡፡

ሐቪስቶ ይህን ያሉት በትላንትናው እለት በአውሮፓ ኅብረት ጠቅላይ ምክር ቤት ‹‹በትግራይ ላይ እየተፈፀመ ላለው የጦር ወንጀል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ወደ ፍርድ የሚቀርቡ ይመስልዎታል ወይ›› በሚል ከአየርላንዱ ተወካይ ጥያቄ በቀረበላቸው ወቅት ነው፡፡

ምላሹን የሰጡት ሐቪስቶ ‹‹በአሁን ሰዓት በርካታ ገለልተኛ ተቋማት እየተፈፀመ ስላለው ግፍና ወንጀል ዝርዝር እያወጡ ቢሆንም፣ የተባበሩት መንግስታት እያካሄደ ያለውን ምርመራ እስኪያጠናቅቅ ብንጠብቅ ይሻላል›› ካሉ በኋላ፣ ‹‹ባለፈው የካቲት የኢትዮጵያ ባለስልጣናትን ባገኘኋቸው ጊዜ የትግራይን ሕዝብ እንደሚያጠፉት፣ እንደሚያወድሙትና 100 ዓመታት ወደ ኋላ እንደሚመልሱት ቃል በቃል ነግረውኛል፣ እንደኔ ሐሳብ ከሆነ ይህ በጦር ወንጀል የሚያስጠይቅ ነው›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ሐቪቶ ይህን ቃል የተናገሩት ባለሥልጣናት የትኞቹ እንደሆኑ የጠቀሱት ነገር የለም፡፡

ባለፉት 6 ወራት ውስጥ ሁለት ጊዜ ወደ አዲስ አበባ መጥተው የነበሩት የፊንላንዱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ፔካ ሐቪስቶ፣ በቆይታቸው ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ ከተለያዩ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ተገናኝተው መነጋገራቸው በወቅቱ ተዘግቦ ነበር፡፡

ፔካ ሐቪስቶ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ተናግረዋል ስላሉት ጉዳይ፣ ይህ ዘገባ እስከተሰናዳበት ሰአት ድረስ በመንግሥት በኩል የተሰጠ ምላሽ የለም፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img