Monday, September 23, 2024
spot_img

በምዕራብ ኦሮሚያ ሁለት አፍጋኒስታናውያን ታገቱ መባሉን የዞኑ ኃላፊ አስተባበሉ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ሰኔ 11፣ 2013 ― በበኦሮሚያ ከልል ምዕራብ ወለጋ መነሲቡ ወረዳ በማዕድን ማውጣት ሥራ ላይ የተሰማሩ ሁለት የአፍጋኒስታን ዜጎች በታጣቂ ቡድን ታግተዋል የተባለው ሐሰት መሆኑን የዞኑ ኃላፊ አስተባብለዋል፡፡

የምዕራብ ወለጋ ዞን ኃላፊ አቶ ኤሊያስ ኡመታ ምላሽ የሰጡት በምዕራብ እና ደቡብ ኦሮሚያ እንደሚቀሳቀስ የሚነገረው ራሱን ‹የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት› የሚለውና መንግሥት ‹ኦነግ ሸኔ› የሚላቸው ታጣቂዎች ሁለት ለማዕድን አውጪ ድርጅት ይሰራሉ ያሏቸውን የአፍጋኒስታን ዜጎችን በመነሲቡ ወረዳ እንዳገቱ መግለጻቸውን ተከትሎ ነው፡፡ ታጣቂ ኃይሉ ታግተዋል ያላቸውን ሰዎች ከነ ፎቷቸው ለጥፎ ነበር፡፡

ሆኖም በአካባቢው ተፈጸመ ስለተባለው እገታ እኚሁ ኃላፊ ድርጊቱ አልተከሰትም በማለት ማስተባበላቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

አስተዳዳሪው አቶ ኤሊያስ ኡመታ ‹‹አፍጋኒስታናዊ እኛ ጋር የለም፤ ዞናችንን በደንብ ነው የምናውቀው›› በማለት ድርጊቱ ስለመፈፀሙ እንደማያውቁ ተናግረዋል።

‹‹የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት›› አሁን ፈጸምኩት ያለው እገታ ሁለተኛው ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም ሦስት በማዕድን ማውጣት ሥራ ላይ ተሰማርተው ነበር ያላቸውን የቻይና ዜጎችን ካገተ በኋላ ለዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር አሳልፎ መስጠቱ መገለጹ ይታወሳል።

በወቅቱ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት እንዲሁም የዞኑም ሆነ የመነሲቡ ወረዳ ባለሥልጣናት ይህ ድርጊት በአካባቢው ስለመፈፀሙ አስተባበለው ነበር።

ነገር ግን ከቀናት በኋላ ግን የዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ሦስቱን የቻይና ዜጎች አዲስ አበባ ለሚገኘው የቻይና ኤምባሲ እንዲሰጡ ማመቻቸቱን በወቅቱ ለሚዲያዎች አረጋግጧል።

ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር ፓርቲ ተገንጥሎ የሚንቀሳቀሰው ይህ ቡድን፣ አገትኳቸው ያላቸው ሁለት ግለሰቦች ‹ሙን ሮክ ማይኒንግ ኤንድ ማርብል ዴቬሎፕመንት› ለሚባለው የደቡብ አፍሪካ ኩባንያ የሚሰሩ ናቸው ብሏል፡፡

ታጣቂው ኃይል በመግለጫው ላይ የታገቱት ግለሰቦች ስም ሰዒድ ሐሺም እና ሰዒድ አቡበከር እንደሚባሉ የገለፀ ሲሆን፣ የግንባሩ የዓለም አቀፍ ቃል አቀባይ ናቸው በተባሉት ኦዳ ተርቢ ስም በተከፈተ ገጽ ላይ የታገቱትን ግለሰቦቹን የደኅንነት ሁኔታን በሚመለከት ‹‹በጥሩ ሁኔታ ላይ ናቸው›› የሚል መረጃ ሰፍሯል።

ፎቶ፡ ‹የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት› ታግተዋል ያላቸው ሁለት ግለሰቦች

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img